ልጆችህን ሀብታም እንዲሆኑ አታስተምራቸው! ደስተኛ መሆንን አስተምራቸው! ያን ስታደርግ ልጆችህ ሲያድጉ የነገሮችን ዋጋ ሳይሆን፣ በህይወት ውስጥ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች አሳምረው የሚያውቁ ይሆናሉ!
ወደ አፍህ የምታስገባውን ምግብ ሁሉ፣ ልክ እንደ መድኃኒት ቆጥረህ፣ በጥንቃቄ እየመረጥክ ብላ፣ ጠጣ! ምግብን እንደ መድኃኒት ሳትቆጥር ሁሉን እያግበሰበስክ ብትኖር.. በመጨረሻ፣ መድኃኒቶች ቋሚ ምግቦችህ ይሆናሉ፡፡ መድኃኒትን እንደ ምግብ እየቃምክ ህይወትህን ታገባድዳለህ!
በሰዎች መካከል ልዩነት መኖሩን ልብ ብለህ አስተውል! አንተን በእውነት የሚወዱህ፣ እና ስላንተ ደስታ የሚጨነቁ ሰዎች፣ ካንተ ጠፍተው አይጠፉም! ባንተ ተስፋ አይቆርጡም! ሁሉነገርህ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ቢያገኙት እንኳ፣ የሆነች ባንተ ተስፋ የሚያደርጉባትን ምክንያት ያገኙ (እና ካንተ ርቀው ያልራቁ) ሰዎችን የከበረውን የልብህን ክፍል ቆርሰህ ሁልጊዜም በደስታህ ሰዓት አስባቸው! ይበልጥ አስጠጋቸው! ሰው ከሰው ይለያል!
አንድ ነገር በጣም ልብ ብለህ አስተውል! ባዶ እጅህን ወደዚህች ዓለም ስትመጣ፣ ገና በእንቦቃቅላነትህ፣ ሁሉም ሰው ወዶህ ነው ጨቅላዋን ዕድሜህን ያለፍካት! ባዶ እጅህን ተወልደህ ሳለ፣ ሁሉም ይወድሃል፡፡ ፍቅርን ያዘንብልሃል፡፡ ይሳሳልሃል፡፡ ምንም ባልነበረህ የህይወትህ ጅማሮ ሰዎች ሁሉ በባዶህ እንደወደዱህ አስታውስ፡፡
ደግሞም ስትሞት ስለመለየትህ ብቻ ብለው ሁልጊዜም አንተን በሀዘኔታና በፍቅር የሚያስቡህ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እመን፡፡ ሁሉን የዚህችን ዓለም ነገር ጥለህ ባዶ እጅህን በሞት ስታሸልብም አንተን በትዝታቸው የሚያስቡ፣ የሚናፍቁ፣ ክፉህን ማየት የማይሹ፣ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ እወቅ፡፡
ሁልጊዜ ሀብት ስላለህ ብቻ፣ በቁሳቁስ ስለተከበብክ ብቻ ሰዎች የሚወዱህ ከመሰለህ፣ እነዚህን ሁለቱን አስታውስ፡፡ በእነዚህ ሁለቱ – በውልደትህና በሞትህ ሰዎች ወደውሃል፡፡ ይወዱሃልም፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ጊዜ እንዳጀማመርህና እንዳጨራረስህ አሳምረህ መጠቀም ያንተ ፋንታ መሆኑንም ሁልጊዜ አስታውስ! በመሐል ባለው መንገድህ ይቺን የቆየች ምክር አትርሳት፡- ‹‹ቅርብ አዳሪ ብቻውን፣ ሩቅ አዳሪ ግን ከሰው ጋር ይሄዳል!››
በመጨረሻም ለሰው ልጆች ሁሉ በፈጣሪ በነፃ የተበረከቱለት፣ እና በምንም ውድ ዋጋ የማይተኩ፣ በዚህ ዓለም ላይ የሚገኙ 6ቱ እጅግ የረቀቁ፣ የመጠቁ ዶክተሮች እነዚህ ናቸው ይለናል፡-
ዶክተር ቁጥር ፩ ፦ የፀሐይ ብርሃን !
ዶክተር ቁጥር ፪ ፦ ዕረፍት !
ዶክተር ቁጥር ፫ ፦ የአካል እንቅስቃሴ !
ዶክተር ቁጥር ፬ ፦ ጤናማ አመጋገብ !
ዶክተር ቁጥር ፭ ፦ በራስ ማመን !
ዶክተር ቁጥር ፮ ፦ ጓደኞች !
ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
t.me/danelroza
ለፌስቡክ
👇👇👇
Fb.com/danelroza
ለሊንክደን ፡
👇🏾👇🏾👇🏾
linkedin.com/in/danelroz
Subscribe to get the latest posts sent to your email.
