ይህን መጽሐፍ ከየትም ፈልጋችሁ አንብቡት። ስለ ኢትዮጵያ ማወቅ ከተፈለገ በጣም ይረዳል። ታላላቆቹ ሀገራት ስለ ኢትዮጵያ ምን ያስባሉ የሚለውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ግብጽ ስለ አባይ ስትል ኃይለ ሥላሴን እስከመግደል ስለማሴሯ፤ ሳይሳካም ሲቀር ኢትዮጵያን የመበተን እቅዷን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በከፊልም ተሳክቷል። ኢትዮጵያ ኤርትራን እንዲሁም ጅቡቲን አጥታለች። በሌላ ቋንቋ ባህር በር የለሽ ትልቅ ሕዝብ ያላት ሀገር ሆናለች። ግብጽ ብቻዋን አልነበረችም። እንግሊዝም፣ አሜሪካም፣ፈረንሳይም… ረድተዋታል።
“የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው እየተባለ ይነገራል።በተመዘገቡት ጦርነቶች ሁሉ ኢትዮጵያ በወራሪነት ዘምታለች የተባለበት አጋጣሚ የለም። ጦርነቶቹ በአብዛኛው የራሳቸውን የፖለቲካና የሃይማኖት ዓላማ ለማስፋፋት፣ በኤኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃርም ለም አፈሯን፣ ጤናማ የዓየር ንብረቷንና የሕይወት ደጋፊ የሆኑ ወንዞቿን ለመቆጣጠር ከሚሹ የውጭ ወራሪዎች የሚሰነዘሩ ነበሩ።የቀሩት ደግሞ በተለያየ ወቅት የተነሱ ገዢዎች ግዛታቸውን ለማስፋትና ሌላውን ወገን ለማስገበር የተካሄዱ የሀገር ውስጥ ዘመቻዎች ናቸው። በተከታታይ ትውልዶች የተከሰቱ የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ዘመቻዎች ሕዝቡን አቀራረቡት፣ አዋሃዱት እንጅ አልበታተኑትም። ሌላው ቀርቶ ለሥልጣን የበላይነት እርስ በርስ በመዋጋት ላይ የነበሩ የክልል ገዢዎች ሀገሪቱን የውጭ ጠላት በሚወርበት ጊዜ ልዩነታቸውን ለጊዜው አቻችለው፣ አንድ ሆነውና ተስማምተው የጋራ ጠላታቸውን በመመለስ የሀገራቸውን አንድነት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት ጠብቀው እንደኖሩ በታሪክ ተመዝግቧል። ከአንዱ የሀገሪቱ ማዕዘን ተነስቶ ወደ ሌላው ማዕዘን የሚዘምተው ተዋጊ በዘመተበት ክልል እየሠፈረ፣ እየተጋባና እየተዋለደ ለሕዝቡ አካላዊና መንፈሳዊ መዋሃድ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።”
“በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜውና ሁኔታው በፈቀደው መጠን መንግስታዊ አስተዳደሩን ዘመናዊ ለማድረግ፣ ትምህርት ለማስፋፋት፣ ማህበራዊ አገልግሎት ለማሟላት ተሞክሯል። ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርም የማይናቅ ውጤት ታይቷል። ይህ ጥረት ዋና ትኩረቱ ሥልጣንን ለማማከል ስለነበር ስለሕዝብ መብትና ነፃነት መከበር፣ ዲሞክራሲንና ዲሞክራሲያዊ አሠራርን ማስረፅ በአጠቃላይም ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን ማረጋገጥ ሳይችል ቀርቷል። በዚህ ክንውን በጊዜው ለሥልጣን የበቃው አብዛኛው ምሁር ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለግል ጥቅም በማደሩ፣ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በሥራ ላይ ቸማያውሉትን ሥልጣን አሰባስበው እንዲያስዙ አስተዋጽኦ አድርጓል። ጃንሆይ ዕድሜ ተጭኗቸው መንቀሳቀስ ባቃታቸው ጊዜ ያለሳቸው ፍቃድና ትዕዛዝ መራመድ ያልለመደው የበላይ አመራር፣ እሳቸው ሲወድቁ አብሮ ወደቀ። የሕዝብ መብት ጥያቄም ተዳፈነ። ዕውቀቱ፣ ሙያው፣ የዘመናዊ ዕድገት ግንዛቤው ያለው ምሁር ከሕዝብ ጎን ሆኖ ካልሠረ ሕዝብ የመብትና የዕድገት ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችልም በተግባር ተረጋገጠ። ” ገጽ 6 እና 7
ያለፈው ዛሬም አላለፈም። “ታሪክ ያስተዋል ከጠቢብ ይልቃል” እንደሚባለው በትናንት መነጽር ውስጥ ዛሬን ማየት ይቻላል። ኢትዮጵያ ዛሬም ጥርስ ውስጥ ገብታለች። ያውም የውስጥም የውጪም ጠላት ክንዱን አስተባብሮ ሊወግራት አሰፍስፏል። ትናንት ኢትዮጵያን ሲሉ የተዋደቁት ልጆች እና የእምነት ተቋማት ተለይተዋል። በልዩነት ሁሉን አቀፍ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። ድምጽ ማፈኛ በተገጠመለት በሚያሳሳቅ መሳሪያ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። አቤት የሚልላቸው ማንም የለም። ይልቁንስ ከመጎዳትና ከመገደሉ በላይ ስላቁ ያማል።
አሁን በስፖንሰር እየሄደ ያለው ሀገሪቱን ለፍርሰት የሚወስደው የቁልቁለት መንገድ ተያይዘነዋል። ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሚያስደነግጥ ሁኔታ የበጀታችን ሸፋኝ ናቸው። ህዝቡ በፈገግታና በአደንዛዥ ወሬ ተደናብሯል። አንዳንድ ልሂቃንም በጥቅምና በሥልጣን ዝምታን መርጠዋል።
በቴሌግራም ይቀላቀሉን
👇👇👇
https://t.me/danelroza
Subscribe to get the latest posts sent to your email.
