7 Oct 2026, Wed

ውስጣችሁ የሚነግራችሁ አንድ ነገር አለ። እርሱንም ማድረግ የምትችሉት እናንተ እንደሆናችሁ ታውቃላችሁ። ስለዚህ ማድረግ ካለባችሁ ማንንም ሳታማክሩ ዝም ብላችሁ አድርጉት። ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ማማከር ይቅርባችሁ። የብዙ ሰዎችን ስህተት አትድገሙ። ጥቂት የማይባል ሰው ምን ያደርጋል? በግሉ የመጣለትን ሀሳብ በሙሉ ለሚመለከተውም ለማይመለከተውም በማጋራት ጊዜውንና ኢነርጂውን ያባክናል። አንድ ስራ መጀመር አስባችሁ እናንተ ያሰባችሁት ስራ እንደማይዋጥለት ከምታውቁት ሰው ጋር ለምን ትወያያላችሁ? እቅዳችሁ የሶሻል ሚድያ ስራ መጀመር ሆኖ ስለሶሻል ሚድያ ምንም እውቀት የሌለው፣ ቪድዮ ከማየት በስተቀር እንዴት እንደሚሰራ ምንም እውቀቱ የሌለው ሰው በምን ሚዛን የእናንትን የContent Creation ሀሳብ እንዲደግፍ ትጠብቃላችሁ? ወደዳችቹም ጠላችሁም ዋናው ጉዳይ ማለቅ ያለበት እራሳችሁ ጋር ነው። ምንም ነገር ለመጀመር ስታስቡ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ወገን ለማስገባት አትቸኩሉ። ብዙ ሰው ባማከራችሁ ቁጥር ብዙ ሀሳብ ታገኛላችሁ የበዛው ሀሳብ ደግሞ ግራአጋብቶ የእናንተን መነሻ ሀሳብ ዋጋቢስ የማድረግ ከፍተኛ እድል አለው።

አዎ! ማንንም አትጠይቁ፣ ከአቅማችሁ በላይ ካልሆነ በቀር ማንንም አታማክሩ። የውሳኔ ሰው ሁኑ፣ ሃላፊነት ውሰዱ፣ ከከሰራችሁም ክሰሩ ትማሩበታላችሁ፣ ከተበላሸም ይበላሽ ድጋሜ በተሻለ መንገድ ትሰሩታላችሁ፣ ከወደቃችሁም ውደቁ ዳግም መነሳት እንደሚቻል ውስጣችሁን አሳምኑት። የዓለም እውነታ ይሔ ነው፣ በጣም ብዙ ሰው በሀሳባችሁ አይስማማም፣ ከምትጠይቁት አብዛኛው ሰው ሀሳባችሁ አይዋጥለትም፣ ሊደግፋችሁም ፍቃደኛ አይሆንም። ስለዚህ ይሔንን እውነታ ተረድታችሁ እቅዳችሁን ማባከንና መና ማስቀረት ካልፈለጋችሁ በስተቀር ድጋሜ እቅዳችሁን ለማንም አታማክሩም፣ ለማንም አትናገሩም። ከማንም በሚመጣ ሀሳብ ለመሞላትም ሆነ ማንም የሚነግራችሁን ሀሳብ ተቀብላችሁ ለመፈፀም ጊዜ የላችሁም። ያላችሁ ጊዜ በጣም ጥቂት ነው። ጊዜያችሁን የእራሳችሁን ሀሳብ ወደ ምድር በማምጣት ተጠቀሙት። ማንንም የማባበል ግዴታ የለባችሁም፣ ማንም እንዲደግፋችሁ የማስገደዱም መብት የላችሁም። ውሳኔው በእጃችሁ ነው። የሚደግፋችሁን ሰው እስክታገኙ ሰዎችን መጠየቃችሁን መቀጠል ወይም በሀሳባችሁ ተማምናችሁ ወደ ተግባር መግባት።

አዎ! ጀግናዬ..! ማንንም ጣልቃ አታስገባ፣ እንዴትም ውጫዊ ግፊትና ጫና ሀሳብህን እንዲያስቀይርህ አትፍቀድ። ሀሳብህን እንደ ሀሳብ በልብህ ያዘው ፣ እቅድ አውጣለት ፣ ከእራስህ ጋር ተማከርበት ፣ አዋጭነትቱን በሚገባ አጥና ፣ በደምብ እወቀው ፣ ግልፅም አድርገው። ላንተ ግልፅ እስከሆነ ፣ አንተ እስከተረዳሀውና አንተ እስካመንክበት ድረስ የማንም ድጋፍ እንደማያስፈልግህ እወቅ። የማያዳግም ቆራጥ ውሳኔ መወሰን ከፈለክ ብዙ ሰው ማማከር አቁም ፣ ሀሳብህን ወደ ተግባር መቀየር ከፈለክ ለማንም ማብራራት ሳይኖርብህ በልበሙሉነት አድርገው። የምታማክረው ሰው ብትወድቅ አብሮህ አይወድቅም ፣ ሀሳብ የምትጠይቀው ሰው ብትከስር አብሮህ አይከስርም ፣ የሚያስፈራራህ ሰው ሃሳብህ መና ቢቀር ካንተ ጋር አይጎዳም። በስተመጨረሻ ከሀሳብህም ሆነ ከውጤትህ ጋር የምትቀረው አንተ ብቻ ነው። በእርግጥ ሰውን ማማከር ትልቅ ጥቅም አለው፣ ነገር ግን የምታማክረው ሰው በሀሳብህ እንደሚስማማና የተሻለ አማራጮችን እንደሚጠቁምህ እርግጠኛ ካልሆንክ ባታማክረው ብታተርፍ እንጂ አትጎዳም። ውስጥህን አዳምጥ፣ እርምጃ ውሰድ፣ ማድረግ ያለብህን በጊዜ አድርግ፣ መውሰድ ያለብህን ትምህርትም በተግባር ውሰድ።

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇🏽👇🏽👇🏽
t.me/danelroza
ለፌስቡክ 
👇🏽👇🏽👇🏽
Fb.com/danelroza
ለኢንስታግራም
👇🏽👇🏽👇🏽
Instagram.com/danelroziye


Discover more from ዳንኤል

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Discover more from ዳንኤል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading