7 Oct 2026, Wed

በእውነት ያልተገነባ ህሊና አይታመንም ፡ በአመክንዮ ያልታነፀ ልብ ዋሾ ነው ፤

{The Science of Becoming Better}

ሰው ሁሉን ነገር ስለማያውቅ በሁሉም ነገር ምክንታዊ ልሁን ቢል አይችልም፡፡ በማናውቀው ነገር ምክንታዊ መሆን አይቻለንም፡፡ ምክንያት የምንደረድረው፣ ማስረጃ የምንቆጥረው፣ አስረጂዎችን የምናቀርበው ነገርየውን ስንገነዘበው ነው፡፡ በማያውቁት ነገር ምክንያት የሚደረድሩ ሰዎች በጨበጣ ቁማር እንደሚጫወቱ ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ለምናውቀው ነገር እንኳን በቂና ትክክለኛ ምክንያት መደርደር መቻል በራሱ ማስተዋል ይፈልጋል፡፡ ብዙ ተምረውና ተመራምረው ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎች የትየለሌ ናቸው፡፡ በጣም ያውቃሉ የምንላቸው ብዙዎቹ ሰዎች ለምክንያታዊነት አይገዙም፡፡ ስለአመክንዮ የሚያስተምሩና የሚደሰኩሩትም ራሳቸው ምክንያታዊ አይደሉም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን?›› የሚለው የሚናገሩትን የማይተገብሩ፤ የሚሰብኩትን የማይኖሩበትን ሰዎችን ለማስጠንቀቅ ነው፡፡ መተንተንና መገንዘብ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ማወቅና ማድረግ አይገናኙም፤ መምሰልና መሆን አንድ አይደሉም፡፡ የሚመስሉ ነገር ግን ያልሆኑ ሺ ናቸው፡፡ በንድፈሃሳብ ደረጃ የምናውቀውን በተግባር ልንቀይረው ስንሞክር የሚከብደን ማወቅና መተግበር የተለያዩ ነገሮች በመሆናቸው ነው፡፡


የዓለማችን ታሪክ በአስቂ፣ በአስደናቂ፣ በአሳዛኝ፣ በግራአጋቢ እና እንግዳ በሆኑ ነገሮቸ የተሞላ ነው፡፡ አይዛክ ኒውተን ህይወቱን በሙሉ የፈላስፋ ድንጋይ (Philosopher’s stone)ን ሲፈልግ ነው የኖረው (የፈላስፋ ድንጋይ ወይም Philosopher’s stone ማለት የኬሚስትሪ፣ የፍልስፍና፣ የሚስጥራዊነት (Mysticism) እና የመንፈሳዊነትን ዕውቀት አጣምሮ የያዘ ጥበብ ነው)፡፡ ኒውተን የፈላስፋን ድንጋይ የሚፈልገው ብረትን ወደወርቅ የሚቀይር የአንጥረኝነት እውቀት ፈልጎ አይደለም፡፡ የእሱ ፍላጎት በዘመኑ የፈላስፋን ድንጋይ ያገኘ ሰው የትኛውንም ህመም የመፈወስና ዕድሜን ለማስረዘም የሚረዳ ጥበብ ባለቤት ይሆናል የሚል እምነትና አስተሳሰብ ስለነበረ ነው፡፡ ቶማስ ኤዲሰንም የራዲዮአክቲቭ (Radioactive) ቴክኖሎጂ የትኛውንም ህመም እንደሚፈውስ ሲናገር ነበር፤ ነገር ግን የቅርብ ረዳቱ የነበረው ክላረንስ ዳሊ (Clarence Dally) የተባለ ሰው በራዲዬሽን ቆስሎና ተሰቃይቶ ከሞተ በኋላ ‹‹ስለራጅ ወይም ስለኤክስሬይ አታውሩኝ፤ እሱን ነገር እፈራዋለሁ›› በማለት ሃሳቡን ቀይሯል፡፡ የአፕል ኩባንያ መስራች የነበረው ስቲቭ ጆብስ ደግሞ አትክልት አዘውትረው የሚመገቡ (Vegan) ሰዎች ዘወትር መታጠብ (regular bathing) አያስፈልጋቸውም ይል ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ሃሳቦች በዘመናዊው ሳይንስ ያልተረጋገጡ ስሁት ሃሳቦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች በሙያቸው የተጨበጨበላቸውና አንቱታን ያተረፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ናቸውና ሁሉን ያውቁ ዘንድ አይችሉም፡፡ ይሄ የሆነው ሰው ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ የትኛውም ሰው የሚያውቀው አንዱን ነገር የሁሉም ነገር መፍትሄ አድርጎ የመመልከት ኢ-ምክንያታዊ አባዜ አለበት፡፡ በዓለማችን የጤና ዶክተሮች ራሳቸውን የሁሉ ነገር አዋቂ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ የህግ አዋቂዎችም የዚህ አመለካከት ሰለባ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚስቶቹም ሐገር የሚያሳድገው የነሱ እውቀት ብቻ እንደሆነ አድርገው ይደሰኩራሉ፡፡ ሁሉም እንደየሙያው ትክክሉ የእሱ ግንዛቤ ብቻ እንደሆነ መናገር የተለመደ ነው፡፡ አዋቂ፣ ምሁር የምንላችው፣ ከተራው ሰው በተለየ የክብር ወንበር የምንስብላቸው ሰዎች በትናንሽ ሃሣቦች ሲወድቁ፤ ኢ-ምክንያታዊ ሲሆኑ ተመልክተናል፡፡ ብዙ የምንጠብቅባቸው፣ ሀገራችንን አደራ የሰጠናቸው ሁሉ አድሏዊ ሆነው ከምክንያታዊ ህግ አፈንግጠው እውነትን ሲጨፈልቁ፣ ፍትህ ላይ ሲረማመዱ አይተን ታዝበናል፡፡


ስለአንድ ነገር ያለን ዕውቀት ስለሁሉም ነገር ዋስትና እንደማይሰጥ ለማወቅ አስተዋይ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ዛሬ ያለን ዕውቀት እንኳን የነገ ዕውቀታችንን አያረጋግጥም፡፡ ዕውቀት ልክ እንደሰው ያድጋል ይመነደጋል፡፡ በትናንትና እና ዛሬ ዕውቀት መኩራራት የማይቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ሰውም ያለፈው ላይ ተጣብቄ እቀራለሁ ቢል ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ አይችልም፡፡ ሁሉም ነገር እንደጅረት ወደፊት ይፈስሳል፡፡ አንድ ወንዝ የተለያየ ውሃ እንደሚያፈስሰው ሁሉ ሰውም የተለያየ ሃሳብ እያስተናገደ ነው ወደፊቱ የሚነጉደው፡፡ ጊዜ የሚያመጣው፤ ጭንቅላት የሚያፈልቀው አዲስ ነገር አያጣም፡፡ ያለፈውን የሚያስረጅ፣ የዛሬውን የሚሽር፣ የዕለቱን የሚያድስ አዲስ ዕውቀት ዕለት ዕለት ይመነጫል፡፡ የእውቀት ምንጩ አይደርቅም፡፡ ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ ሄራክሊተስ ‹‹ተፈጥሮ በማያቋርጥ ፍሰት ውስጥ ነው ያለው፣ ዓለም እንደጅረት ቁልቁል ይፈስሳል›› ብሎ ያምናል፡፡ የሰው ዕውቀቱ፣ ሃሳቡ፣ ስሜቱ ወጥ በሆነ መንገድ ይለዋወጣል፡፡ መለዋወጥ ቋሚ ተፈጥሮው ነው፡፡ ጊዜ ሊያቆመው ወይም ሊመልሰው አይችልም፡፡ ሄራክሊተስ ‹‹ማንም አንድን ወንዝ ሁለት ጊዜ ሊሻገር እንደማይችለው ሁሉ ሰውም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አይኖረውም፡፡ የወንዙ ውሃ አንድ እንዳልሆነ ሁሉ ሰውም አንድዓይነት ሆኖ አይቀጥልም (“No man ever steps in the same river twice, for it’s not the same river and he’s not the same man”)፡፡›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡


ወዳጄ ሆይ… ሃሳብ ወላዋይ ነው፤ ስሜት አሳሳች ነው፡፡ ሕሊና አስመሳይ ነው፤ ውሸቱን እውነት አስመስሎ ያቀርባል፡፡ ደመነፍሳቸውን ብቻ ተከትለው ገደል የገቡ መዓት ናቸው፡፡ የገዛ ፍላጎታቸው ያጠፋቸው ተቆጥረው አያልቁም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ለኢጓችን የሚስማማ ሃሳብ እስካገኘን ድረስ እውነትና አመክንዮን ረግጠን እንረማመድበታለን፡፡ እውነት ከሚሰጠን ይልቅ ስሜት የሚሰጠንን እናምናለን፡፡ ደስታን ብቻ ስናሳድድ ሰላም፣ ፍትሐዊነትና እውነት ያመልጡናል፡፡ ሰላም በደስታ ውስጥ እንደማይገኝ አይገባንም፡፡ ደስታ ቅፅበታዊ ነው፤ ሰላም ግን ቋሚ ነው፡፡ ከደስታ ይልቅ ሰላምን የያዘ ህይወቱ ብሩህ፣ አዕምሮው ንፁህ ይሆናል፡፡ ሰላም ከእውነት፤ ደስታ ከስሜት የሚወለዱ ናቸው፡፡ ሰላም የሌለው ደስታ አለ፤ እውነት የሌለው የአዕምሮ ሰላም ግን አይኖርም፡፡ የአዕምሮና ሰላምና የልብ ደስታ ስሙም የሚሆኑት እውነት ሲኖራቸው ነው፡፡ ያልተፈተሸ ሃሳብ፣ ልቅ ፍላጎትና ያልሰከነ ስሜት አደጋው ብዙ ነው፡፡ ውስጥህ የነገረህን ብቻ ማመን ጥሩ አይደለም፡፡ ዓይንህ ያየው፣ ጆሮህ የሰማው፣ አፍንጫህ የማገው፣ ምላስህ የቀመሰው፣ እጅህ የዳሰሰው፣ ደመነፍስህ ሹክ ያለህ ሁሉ እውነት አይደለም፡፡ መጣራት፣ መፈተሸ፣ ጥሬና ብስሉ መለየት፣ መበጠር፣ ሃሳቡን ማንከሽከሽ፣ ስሜቱን አስክኖ ጥቅምና ጉዳቱን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ውስጥህን ማመን ደረጃ ላይ የምትደርሰው ለውስጥህ የተለያየ ሃሳብ ስትመግበውና በእውነት፣ በምክንያት፣ በፍትህና በሰላም ስትገነባው ነው፡፡ በእውነት ያልተገነባ ህሊና አይታመንም፤ በአመክንዮ ያልታነፀ ልብ ዋሾ ነው፡፡
ምክንያታዊ ሕሊና፤ አመዛዛኝ ልቦና!

ቸር ጊዜ !

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇🏽👇🏽👇🏽
t.me/danelroza
ለፌስቡክ 
👇🏽👇🏽👇🏽
Fb.com/danelroza
ለኢንስታግራም
👇🏽👇🏽👇🏽
Instagram.com/danelroziye


Discover more from ዳንኤል

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Discover more from ዳንኤል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading