ፍልስፍናን ከተዋወኳት ጊዜ ጀምሮ ካነበብኳቸው መጽሃፍት ውስጥ ማንኛውም ጥልቅ ሃሳብ ያለው ሰው ሊያነባቸው ይገባል ብዬ የማስባቸውን ምርጥ እስር መጽሃፍት ልጋብዛችሁ።
እንግዲህ በሁሉም ትውልድ ውስጥ፣ ከመዝናኛነት ባለፈ ትልቅ ትርጉም ያላቸው መጽሐፍት አሉ። እነዚህ መጽሐፍት የለመድናቸውን አስተሳሰቦች ይሞግታሉ፣ ቅዠቶችን ያፈርሳሉ፣ የማይመቹ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፣ እንዲሁም እራሳችንን እና ዓለምን የምንረዳበትን መንገድ ይለውጣሉ። እነዚህ የምጋብዛችሁ አስር መጽሃፍት ዝም ብለው የሚነበቡ መጽሐፍት ብቻ አይደሉም፤ የሰውን ልጅ የአስተሳሰብ አቅጣጫ ሊቀይሩ የሚችሉ የእውቀት ማዕበሎች ናቸው።
ፈላስፋ፣ ተማሪ፣ ጸሐፊ፣ ወይም ዝም ብሎ ጥልቅ አስተሳሰብን የሚወድ ሰው ከሆናችሁ እነዚህ መጽሐፍት በመደርደሪያችሁ ላይም በአእምሯችሁ ውስጥም ቦታ ሊኖራቸው ይገባል።
1. The Republic — ፕላቶ
ይህ መጽሃፍ ምናልባትም በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ስራ ሊሆን ይችላል። በሶቅራጥስ አንደበት፣ ፕላቶ ስለ ፍትህ፣ እውነት፣ ፖለቲካ፣ ትምህርት እና ስለ እውነታ (reality) ምንነት የሚመረምርበት ስራ ነው። እስካሁን ድረስ የሰው ልጅ ስለ አላውቂነትና እና እውቀት ካሰፈራቸው ታላላቅ ምልከታዎች አንዱ የሆነው ታዊቂው ‘የዋሻው ምሳሌ’ (Allegory of the Cave) የሚገኘውም በዚህ ድንቅ መጽሃፍ ውስጥ ነው
ለምንድን ነው ይሄን መጽሃፍ ማንበብ ያለብን ካላችሁኝ ምክንያቱም እያንዳንዱ አሳቢ ሰው ውሎ አድሮ ፍትህ ምንድን ነው? እውነትስ ምንድን ነው? እንዲሁም እውነተኛውን ነገር ከቅዠት እንዴት እንለያለን? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳቱ አይቀርምና እላቸሃለው።
2. Meditations — ማርከስ ኦሪሊየስ
በሮማዊው ንጉሠ ነገሥት እንደ ግል ማስታወሻ የተጻፈው ይህ ዘመን አይሽሬ ስራ፣ ስለ ራስ-ስርዓት (self-discipline)፣ ስቃይ፣ ሟችነት እና ውስጣዊ ነፃነት ጥልቅ ግንዛቤዎችን የሚሰጥ መጽሃፍ ነው።
ለምን እናንባብበው ካላችሁኝ ምክንያቱም ህይወት እኛን ከችግር ጋር ማጋፈጧ አይቀርም፤ ከዚህ መጽሃፍ በተሻለ ስለ ጽናት እና ክብር የሚያስተምሩ መጽሃፍት ጥቂት ናቸውና እላቹሃለው።
3. Critique of Pure Reason — ኢማኑኤል ካንት
እስካሁን ካነበብኳቸው መጽሐፍት ውስጥ እጅግ ጠቃሚ እና ለመረዳት ከባድ ከሆኑት መካከል አንዱ ይህ መጽሃፍ ነው። በዚህ ስራ ውስጥ ካንት የሰውን ልጅ የእውቀት ገደብ ይመረምራል፤ እንዲሁም ስለ እውነታ በእውነት ምን ማወቅ እንደምንችል ይጠይቃል።
ለምንድን ነው መነበብ አለበት ካላችሁን ምክንያቱም ዓለምን ከመረዳታችን በፊት፣ ዓለምን ለመመልከት (perceive ለማድረግ) እና ለመተርጎም የምንጠቀምባቸውን መሳሪያዎች መረዳት ስላለብን ነው እላቹሃለው።
4. Thus Spoke Zarathustra — ፍሪድሪክ ኒቼ
ይሄ ከፊል ፍልስፍና፣ ከፊል ግጥም፣ እና ከፊል ትንቢት የሆነ የጀርመናዊው ፍሬድሪክ ዊልሄልም ኒቼ (My favorite philosopher of all time) ስራ ነው። በዚህ ስራው ውስጥ ኒቼ ባህላዊ የሞራል እሴቶችን፣ የሃይማኖት ዶግማዎችን እና የአስተሳሰብ ተገዥነትን ይሞግታል፤ ጎን ለጎን ደግሞ አዳዲስ እሴቶች እንዲፈጠሩ ጥሪ ያቀርባል።
ለምን እናንብበው ካላችሁኝ ምክንያቱም የድሮ እርግጠኛነቶች (እምነቶች) ከፈረሱ በኋላ “እንዴት መኖር አለብን?” የሚለውን ጥያቄ እንድንጋፈጥ ስለሚያስገድደን እላቹሃለው።
5. The World as Will and Representation — አርተር ሾፐንሃወር
ይሄ ስለ ፍላጎት፣ ስቃይ እና ስለ ህልውና እረፍት አልባ ተፈጥሮ የተደረገ ጥልቅ ፍለጋ ነው። ሾፐንሃወር በዘመናዊ ፍልስፍና፣ ሳይኮሎጂ እና ስነ-ጽሑፍ ውስጥ ተጽዕኖ ያሳደረ ድንቅ ፈላስፋ ነው።
ለምን እናንብበው ካላችሁኝ የሰው ልጆች ለምን እንደሚሰቃዩ ከተጻፉት እጅግ ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎች አንዱ ስለሆነ እላቹሃለው።
6. Beyond Good and Evil — ፍሬድሪክ ኒቼ
በዚህኛው መጽሐፉ ኒቼ በተለመደው የሞራል እይታ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ይሰነዝራል፤ እንዲሁም አንባቢዎች ተቀባይነት ካገኙ እውነታዎች በስተጀርባ የተደበቁትን ውስጣዊ ግፊቶች እንዲመረምሩ ይጋብዛል።
ለምን እናንብበው ካላችሁኝ እውነተኛ አስተሳሰብ የሚጀምረው ሌሎች ሰዎች ሁሉ ያለምንም ጥያቄ የሚቀበሏቸውን ሃሳቦች መጠየቅ ስንጀምር ስለሆነ እላቹሃለው።
7. On the Genealogy of Morality — ፍሬድሪክ ኒቼ
ይሄ ስለ ሞራል እሴቶች አመጣጥ የተደረገ ፍልስፍናዊ ምርመራ ነው። ኒቼ ሞራል እውነት ነው ወይስ አይደለም ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ከየት መጣ እና የማንን ፍላጎት ያገለግላል የሚለውን የመረመረበት ድንቅ ስራ ነው።
ለምን እናንብበው ካላችሁኝ የእሴቶችን ታሪክ መረዳት እራሳችንን እንድንረዳ ስለሚያግዘን እላቹሃለው።
8. Fear and Trembling — ሶረን ኪርኬጋርድ
ይህኛው ኬርኬጋርድ ስለ እምነት፣ ጭንቀት፣ ግለሰብነት፣ እና የሰውን ልጅ ህይወት ስለሚተረጉሙ ከባድ ምርጫዎች የጻፈው ድንቅ ስራ ነው።
ለምን እናንብበው ካላችሁኝ በህይወት ውስጥ አንዳንድ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች በሎጂክ (በምክንያታዊነት) ብቻ ሊወሰኑ ስለማይችሉ በቀጥታ ወደ ሕልውና እንድናይ ስለሚረዳን እላቹሃለው።
9. Civilization and Its Discontent — ሲግመንድ ፍሮይድ
ፍሮይድ በሰው ልጅ ደመነፍስ (instincts) እና ስልጣኔ በሚጠይቃቸው ነገሮች መካከል ያለውን ውጥረት የመረመረበት ስራ ነው። በዚህ መጽሃፍ ውስጥ ያሰፈራቸው ምልከታዎቹ ዛሬም ስለ ባህል እና ሳይኮሎጂ በሚደረጉ ክርክሮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።
ለምን እናንብበው ካላችሁኝ በግለሰብ ፍላጎቶች እና በማህበራዊ ስርዓት መካከል ያሉትን የተደበቁ ግጭቶች ስለሚመረምር ጠቃሚ ነው እላቹሃለው።
10. The Structure of Scientific Revolutions — ቶማስ ኩን
ይሄ ሳይንሳዊ እውቀት እንዴት እንደሚለወጥ የሚያሳይ አብዮታዊ ጥናት ነው። ኩን የአእምሯዊ እድገት አብዛኛውን ጊዜ እውነታዎችን በማከማቸት ብቻ ሳይሆን፣ በመሰረታዊ የአመለካከት ለውጦች (paradigm shifts) የሚመራ መሆኑን ያሳየበት ትልቅ ስራ ነው።
ለምን እናንብበው ካላችሁኝ በጣም የምናምናቸው የእውቀት ስርዓቶቻችን እንኳን በታሪክ የተቃኙ እና ለለውጥ የተጋለጡ መሆናቸውን ስለሚያስተምረን እላቹሃለው።
እነዚህ አስር መጽሐፍት አንድ ወጥ የሆነ ፍልስፍና የላቸውም። እንዲያውም፣ አብዛኛዎቹ እርስ በርሳቸው በጥልቀት የሚጋጩ ናቸው። ሆኖም ግን አንድ ላይ ሲጣመሩ፣ ስለ እውነታ፣ እውቀት፣ ሞራል፣ ስቃይ፣ ነፃነት፣ ማህበረሰብ እና ስለ ህይወት ትርጉም አስደናቂ የሆነ ውይይት ይፈጥራሉ።
እነዚህ መጽሃፍቶች ያላነበባችሁ ስታነቧቸው የመጨረሻ መልሶችን ለማግኘት ሳይሆን የተሻሉ ጥያቄዎችን እንዴት መጠየቅ እንደሚቻል ለመማር አንብቧቸው። ምክንያቱም ፍልስፍና የሚጀምረው እርግጠኛነትን ስናገኝ አይደለም። የሚጀምረው ለመጠራጠር፣ ለመመርመር፣ እና በራሳችን ለማሰብ የሚያስችል ድፍረት ስናዳብር ነው።
ያነበባቹሃቸው ደግሞ ከነዚህ ውስጥ የትኞቹን መጽሃፍት አንብባቹሃል? እንዴትስ አገኛችሗቸው? ሃሳባችሁን አጋሩን እንወያይበት!!
ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
t.me/danelroza
ለፌስቡክ
👇👇👇
Fb.com/danelroza



Subscribe to get the latest posts sent to your email.
