10 Apr 2026, Fri

የበታችነት ስሜትን የማሸነፊያ መንገዶች ፤

   ማንም ከበታችነት ስሜት ጋር የተወለደ ወይም የሚወለድ ሰው የለም፡፡ የበታችነት ስሜት ተፈጥሮአዊ ሳይሆን በአካባቢ ተጽእኖ የሚመጣ ውጤት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሰዎች ስለራሳቸው የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው ከአካባቢያቸው ይማራሉ፡፡ የተማሩትን ነገር ደግሞ ትተው፣ አዲስ ነገር መማር ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የበታችነት ስሜት ሊለወጥ የሚችል አስተሳሰብ ነው፡፡

እያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮ እንዲሁም ካደገበት አካባቢ አንጻር ልዩ በመሆኑ የበታችነት ስሜትን የሚያሸንፍበት አንድ ወጥ የሆነ አካሄድ ላይኖር ይችላል፡፡ ሆኖም በዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከዚህ በታች የተጠቀሱ ምክሮችን ተግባራዊ ቢያደርጉ ስለራሳቸው ጤናማ/ትክክለኛ የሆነ እይታ ሊያሳድጉ ይችላሉ፡፡

➊ በሌሎች ሰዎች አስተያየት ላይ ጥገኛ አለመሆን

በልጅነት ወቅት አንድ ነገር ሰርተን ፣ ወላጆቻችን ወይም ትልልቆች ብለን የምናስባቸው ሰዎች ጥሩ ነው፣ ትክክል ነው፣ ጎበዝ .… እንዲሉን እንፈልጋለን፡፡ በጎልማሳነት ጊዜ እንዲህ ያለውን የልጅነት ወቅት ባህርይን መተው አስፈላጊ ነው፡፡ ከሰዎች ተገቢውን አስተያየት መጠየቅና ስራችንን መገምገም ጠቃሚ ቢሆንም፣ በእነርሱ አስተያየት ላይ ጥገኛ መሆን  ዞሮ ዞሮ ለራሳችን ያለንን አመለካከት ይጎዳል፡፡

➋ ራሳችንን ከአሉታዊ አስተሳሰቦች መለየት

በተቻለ መጠን ራሳችንን/ ማንነታችንን በአእምሮአችን ውስጥ ከተከማቸው አሉታዊ አስተሳሰብ መለየት አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር በእነዚያ አሉታዊ አስተሳሰቦች ራሳችንን መመዘን ስንተው ፣ እነዚያ አስተሳሰቦች ኃይል ያጣሉ፡፡ በእርግጥ ከእኛ ጋር ለረጅም ጊዜ የቆዩ ከሆኑ፣ ከእነርሱ ጋር ዝምድና ስለፈጠርን በቀላሉና ቶሎ ላይሄዱ/ላይለዩን ይችላሉ፡፡ ሆኖም ከእነርሱ ጋር ላለመኖር ከወሰንን፣ ቀስ በቀስ ስፍራውን ይለቃሉ፡፡ በእነርሱ ስፍራ ደግሞ ተገቢ የሆኑ ሃሳቦችን እናስገባለን፡፡ እነዚያ ቀስ በቀስ ገብተው ስፍራ እንደያዙ ሁሉ፣ አዲሱና መልካም የሆነው አስተሳሰብም ዕድል ከሰጠነው ቀስ በቀስ ወደ አእምሮአችን ገብቶ ሥፍራውን ይይዛል፡፡

➌ በውድቀታችን ራሳችንን ከመኮነን ከውድቀታችን መማር

ስህተት የማይፈጽም ሰው የለም፡፡ ልዩነት የሚያመጣው ስህተታችንን የምናስተናግድበት ሁኔታ ነው፡፡ በስህተታችን ራሳችንን እየወቀስን የምንሄድ ከሆነ፣ ራሳችንን ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ ከስህተታችን ተምረን ወደፊት ማሻሻል የሚገባንን ነገር የምናስብ ከሆነ ደግሞ ራሳችንን ተቀብለን ወደፊት እንሄዳለን፡፡ ስለሆነም በህይወታችን በእኛም ሆነ በሌሎች ሰዎች በደረሰቡን ችግሮች፣ ውድቀቶች፣ አለመሳካቶችና መልካም ያልሆኑ ነገሮች ሁሉ ራሳችንን እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ከመኮነን፣ ከክፉ ነገሮች መልካምን ነገር ተምረን ወደፊት መሄድ የተሻለ አማራጭ መንገድ ነው፡፡

➍ ራሳችንን በፉክክር ውስጥ አለማስገባት

እያንዳንዱ ሰው ልዩ ሆኖ የተፈጠረ ፍጡር ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለው እምቅ ችሎታ አንድ ዓይነት ላይሆን ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ያደገበትና ያለበት ዓውድ ልዩነት አለው፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ጋር ሁልጊዜ መፎካከርና ራሳችንን ከሌሎች አንጻር ከመገመት ይልቅ እኛ ዘንድ ያለውን መልካም ነገር በመለየት በተሻለ መንገድ መጠቀም የምንችልበትን መንገድ መቀየስ ይረዳናል፡፡ ከሌሎች ሰዎች ስኬት፣ ብርታት፣ መልካም ነገሮች፣ አሸናፊነት ለራሳችን መልካም ቁምነገሮችን መማር እንችላለን፡፡ ስለዚህ የፉክክር የህይወት ዘይቤን በመተው ከሌሎች መማርን መልመድ ጠቃሚ ነው፡፡

➎ ስጦታችንን በመለየት ማሳደግ

እያንዳንዱ ሰው ስጦታ እንዳለው ሁሉ እኛም ስጦታ አለን፡፡ ስለዚህ በውስጣችን ያለውን እምቅ ችሎታ፣ ፍላጎታችንንና ምቹ ሁኔታዎችን በመለየት ስጦታችንን በዕውቀትና በክህሎት ማሳደግ እንችላለን፡፡ ጎበዝ በሆንበት ወይም መስራትና መሆን በምንፈልገው ጉዳይ ላይ የበለጠ ዕውቀትና ክህሎትን በማጎልበት የበለጠ ፍሬያማ መሆን እንችላለን፡፡  በችሎታችን ራሳችንና ሌሎች ሰዎችን መጥቀም ስንችል ደግሞ እርካታና ደስታን እናገኛለን፡፡ ለሰዎችም አንድ በጎ ነገር ማድረግ መቻላችን ደግሞ ስለራሳችንም በጎ አስተሳሰብ እንዲኖረን ያግዘናል፡፡

➏ ባለሙያን ማማከር

እንግዲህ ራሳችንን የመቀበል ችግር ሲኖረን በአብዛኛው ከበጎ ነገር ይልቅ በህይወታችን ውስጥ ባሉ ድክመቶች፣ ጉድለቶችና ስህተቶች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ የበታችነት ስሜት መንስኤ የሆኑ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ ተገቢውን መፍትሔ ለመፈለግ እጅግ ያግዛል፡፡ ምክንያቶቹ ከሰው ወደ ሰው የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ራሳችንን የማንቀበል ከሆነ እኛው ለራሳችን ጠላቶች ሆንን ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ ከራሳችን ጋር እንጣላለን፡፡ ጠላትን በውስጣችን ተሸክመን እንዞራለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችንን በመቀበል በሰላም በመኖር የበታችነት ስሜትን ማስወገድ እንችላለን!

➐ ገንቢ ያልሆኑ መንገዶችን መተው

በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንዲሁም ስለራሳችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን እንከን የለሽ ስራዎችን ለመስራት ጥረት ማድረግ የማይጠቅም አካሄድ ነው፡፡ ማንም ሰው በንግግሩና በስራው ፍጹም መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህን ዓይነት መንገድ መከተል የበለጠ ራስን ለውድቀት ብሎም ለበለጠ የበታችነት ስሜት እንዲሰማን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይሆናል፡፡

በቅናት መንፈስ ውስጥ ሆኖ ከሌሎች ሰዎች በልጦ ለመገኘት ጥረት ማድረግ የበታችነት ስሜትን አያጠፋም፡፡ ጤናማ ያልሆነ ፉክክር በማሸነፍና በመሸነፍ ሚዛን ውስጥ ያስገባናል፡፡

ብዙ ጊዜ በአሉታዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ የበታችነት ስሜታችን እንዲኖር እንዲሁም እንዲያድግ ያደርጋል፡፡

ከሌሎች ሰዎች በችሎታ ፣ በብቃት ፣ በትምህርት ደረጃ ፣ በገንዘብና በሌሎች ነገሮች እኩል ብንሆን ስለራሳችን ያለን አስተሳሰብ በጎ እንደሚሆን ማሰብ ሁልጊዜ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ ትኩረት መደረግ ያለበት ደረጃን በማሻሻል ላይ ሳይሆን በማንኛውም ደረጃ ላይ ብንሆን ራሳችንን ተቀብለን መኖር መማር ላይ ነው፡፡ ስለራሳችን ያለንን አሉታዊ ስሜት ማስወገድ ይገባናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *