10 Apr 2026, Fri

አብዛህኞቻችን የተከረቸምንበት አንድ የሆነ ሳጥን አለ ፤
እምቅ ችሎታችንን የገደበ የፈጠራ ችሎታችን ያዳከመ እና ህልሞቻችንን እንዳንኖር ገድቦ የያዘን ሳጥን።

ይህ ሳጥን ህብረተሰቡ ባስቀመጠልን መስፈርት ፣ በራስ አለመተማመን ወይም ባለፉ ውድቀቶች ምክንያት ሊፈጠር ይችላል።

ጥሩ ዜናው ከዚህ ሳጥን ነፃ የመውጣት እና በራስህ ፍላጎት የመኖር ኃይል አለህ። እንዴት እንደሆነ እነሆ ፡

፩. ገድቦ የያዘንን ሳጥን እንወቀው

ከማንኛውም ሳጥን ለመውጣት የመጀመሪያው እርምጃ አንተ በየትኛው ሳጥን ውስጥ እንዳለህ ማወቅ ነው። ይህ ቀላል ሊመስል ይችላል ፣ ግን ጥልቅ የሆነ ራስን ማወቅን ይጠይቃል።

የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህን ፣ ሀሳቦችህን እና ስሜቶችህን ገምግም። አንተን በማይጠቅም ጥለት (pattern) ውስጥ ተጠፍንገሃል? የጎደለህ ነገር እንዳለ ወይም የተገደብክ እንደሆነ ይሰማሃል ? እነዚህን ስሜቶች መቀበል ወደ ለውጥ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

፪. ራስን ማወቅ እና ደፋር መሆን

ከሳጥኑ ውስጥ መውጣት ድፍረትን ይጠይቃል። ፍርሃታችሁን መጋፈጥ እና ወደማይታወቅ ሌላ ነገር ውስጥ መግባት ማለት ነው። የምር ለአንተ አስፈላጊ የሆነውን ነገር እራስህን በመጠየቅ ጀምር።

የአንተ ዋና እሴቶች (values) እና ፍላጎቶች (passions) ምንድን ናቸው? ድርጊቶችህን ከእሴቶችህ ጋር ስታስተካክል እውነተኛ አኗኗር መኖር ትጀምራለህ። ይህ ነፃነትህን የገደቡህን ድንበሮች ለማለፍ እና አዳዲስ እድሎችን ለማሰስ ጥንካሬ ይሰጥሃል።

፫. የሚገድቡ እምነቶችህን ተገዳደራቸው { Challenge your limiting beliefs }

ብዙውን ጊዜ፣ እራሳችንን የምናገኝባቸው ሳጥኖች ከራሳችን ውስን እምነቶች የተገነቡ ናቸው። እነዚህም “እኔ አልችልም” እና “በቂ አይደለሁም” አይነት ገድበው የሚይዙን አስተሳሰቦች/እምነቶች ናቸው። ትክክለኛነታቸውን በመጠየቅ እነዚህን እምነቶች ተገዳደራቸው።

እንደ “እችላለሁ” እና “አቅሙ አለኝ” በመሳሰሉ አዎንታዊ አስተሳሰቦች/እምነቶች ተካቸው።

አስታውስ አእምሮህ ተአምረኛ መሣሪያህ ነው ፤ ግድግዳ ሳይሆን ድልድይ ለመሥራት ተጠቀምበት !

፬. ወደ ለውጥ የሚመሩህን ትንንሽ እርምጃዎች ውሰድ

“የአስተሳሰብ ለውጥ ልክ እንደጓሮ አትክልት እንክብካቤ እና ጊዜ ይፈልጋል። ጊዜ መውሰድ መቻል አለብህ። ብዙ ጊዜ አይቻልም የምንለው ጊዜን ከስሌት ውስጥ ስለምናስወጣው ነው ፤ የሰው አዕምሮ በአንድ ቀን ስላልተሰራ በአንድ ቀን አይቀየርም።

የሰው አእምሮ በስብሰባ ስላልተሰራ በስብሰባ አይቀየርም። የሰው አእምሮ በዘመቻ ስላልተሰራ በዘመቻ አይቀየርም።
    የቁጥር ፬ ሃሳብ ከ ዶ/ር ምህረት ደበበ

በአንድ ሌሊት ከባድ ለውጦችን ማድረግ የለብህም። በትናንሽ እና ልትቆጣጠራቸው በምትችላቸው እርምጃዎች ጀምር። ወደምትፈልገው ውጤት የሚያቀርቡህን ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን አዘጋጅ።

በለውጥ መንገድህ ላይ እያንዳንዱን ትንሽ ድልህን አክብራቸው (Celebrate each small victory)። እነዚህ ቀስበቀስ የሚመጡ ለውጦች ፍጥነትህን እና በራስ መተማመንህን ይገነባሉ፣ ይህም ከሳጥኑ ውስጥ ለመውጣት የምታደርገውን ትልቁን ዝላይ ብዙም አስፈሪ እንዳይሆን ያደርገዋል።

፭. መነሳሳትን በሚፈጥሩልህ እና ድጋፍ በሚያደርጉልህ ሰዎች ራስህን ክበብ

ከራሳቸው ሳጥን ነፃ የወጡ እና ታላቅነትን ያስመዘገቡ ግለሰቦች ታሪኮችን አንብብ። #ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት እንደ ሰነፍ ተማሪ ይቆጠር የነበረውን የአልበርት አንስታይንን ወይም ትልቅ የህይወት ፈተናዎችን በማሸነፍ ዓለም አቀፋዊ ተምሳሌት ለመሆን የበቃችውን የኦፕራ ዊንፍሬይ ታሪክን አንብብ።

የእነሱ የነፃነት ጉዞ አንተም መሰናክሎችን ማሸነፍ እና ህልምህን ማሳካት እንደምትችል እንደ ተምሳሌትነት ሊያገለግሉህ ይችላሉ።

፮. ጽኑ እና በቀላሉ የማይበገር ሰው እንሁን

ከሳጥኑ ውስጥ መውጣት የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም። ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው። በመንገዱ ላይ ችግሮች እና መሰናክሎች ይኖራሉ። በጽናት እና ያለመበገር  ጉዞህን ቀጥል። ራእይህን ግልጽ አድርገው፤ ግቦችህን በየእለቱ ልታያቸው በምትችለው መልኩ በእይታህ ውስጥ አስቀምጥ።

አስታውስ የምትወስደው እያንዳንዱ እርምጃ፣ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን፣ ወደ የተሻለ እርካታ ወደምታገኝበት እና ነጻ የሆነ ህይወት የሚያደርስህ እርምጃ ነው።

፯. ነፃነትህን አክብር { Celebrate Your Freedom}

አንዴ ከሳጥኑ ነፃ ከወጣህ በኋላ አዲስ የተገኘውን ነፃነትህን ለማክበር ጊዜ ውሰድ። የመጣህበትን ጉዞ አስብና ምን ያህል እንደተጓዝክ ራስህን አድንቅ። ለማደግ እና አዳዲስ የህይወት አድማሶችን ማሰስን ለመቀጠል ይህንን ልምድ መሰረት አድርገው።

እንደ መውጫ

ካለህበት ሳጥን በፍጥነት ለመውጣት ገደቦችህን ማወቅ ፣ እምነትህን መገዳደር እና የበለጠ እርካታ ወዳለበት ህይወት የሚወስዱ እርምጃዎችን መውሰድ ነው።
ይህም ትክክለኛ ማንነትህን ማግኘት እና እውነተኛ ህይወትን መኖር ነው። ስለዚህ በጥልቀት ተንፍስ ፣ ድፍረትህን ሰብስብና ከሳጥኑ ውስጥ ለመውጣት እርምጃ ውሰድ።

ከታጠርክበት ሳጥን በፍጥነት ውጣ !

የአስተሳሰብ ሳጥን ነው? ወጣ በልና ተመልከተው።

የሙያ ሳጥን ነው ? ወጣ በል ፤

የኑሮ ሳጥን ነው ? ከእሱም ውጣ ፤

የዕድሜ ሳጥን ነው ? ከእርሱም ውጣ ፤

ከተከረቸምክበት የህይወት ሳጥን ለመውጣት ቢያንስ ሳጥኑን ሳትቧጥጥ ኖረህ ፣ የሞት ሳጥን ፊትህ ሲቀርብ ማየት እጅግ አስከፊው የህይወት መራር ሽንፈት ይህ ነው።

ራሳችንን እንፈትሽ ፡ ራሳችንን እንመልከት።

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም

t.me/danelroza
ለፌስቡክ

fb.com/danelroz
ለሊንክደን

linkedin.com/in/danelroz

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *