የሞቱ የመጨረሻ ቀን ዶስቶይቭስኪ ለወንድሙ ሚካኤል ዶስቶይቭስኪ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ላከለት።
ወንድሜ የኔ ምርጥ ጓደኛ፤ እንግዲህ የእኔ እጣ ፋንታ ተወስኗል። በሳይቤሪያ እስር ቤት የአራት አመት ከባድ የጉልበት ስራ ቅጣት ተጣለብኝ። ከእስር ቤትም ከወጣው በኋላ ለስድስት አመታት የመጻፍ መብቴ ተነፍጎ ወታደር እሆናለሁ።
ታሪኩን ከጅምሩ ልንገርህ ወደ ቤተመንግስቱ አደባባይ ወሰዱን። በዚያም የሞት ፍርዳችን ተነበበ። ቀጥሎም መስቀሉን እንድንሳለመው አዘዙን። አንገታችንን እንዳቀረቀርን አለቅን ብለን ሰይፋችንን ከራሳችን በላይ ከመጣላቸው በፊት። ለመጨረሻ ግዜ ገላችንን ታጥበን ንጹህ ልብስ ለብሰን ነበር።
ከዚያ ግን ሶስት ሶስት አድርገው አስምረው አቆሙን። እኔ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ነበርኩ። በሁለተኛው ምድብ የጥይቱን አፎት ቀማሽ ነኝ ማለት ነው። ለመኖር አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረኝ የምሬን ነው የምልህ ወንድሜ በዛች ቅጽበት ከሌላ ግዜ በተለየ መልኩ አሰብኩህ፤ በጣም ነበር የናፈቅከኝ። በምናቤ ውስጥ አንተ ብቻ ነበር የምትመላለሰው። የእኔ ውድ ወንድም በዛች የመጨረሻ ሰዓት እንዴት እንደምወድህ ነው የገባኝ።
መጥተ እንድታየኝ ስጠይቃቸው እንደማይቻል ነግረውኛል። የተፈቀደልኝ የመጨረሻ ደብዳቤ ለምፈልገው ሰው እንድልክ ነው። እኔ ደግሞ የምፈልገው የሚፈልገኝ የሌለኝ ከንቱ ሰው ነኝ። ያለኸኝ ብቸኛ ወንድም አንተ ብቻ ነህ። የሞት ፍርድ እንደተፈረደብኝ ማወቅህ አስፈርቶኛል። ወደ አደባባዩ በሚወስደኝ የሰረገላ አጥር መስኮት ስመለከት በመንገድ ላይ ብዙ ህዝብ ቆሟል።
ነገር ግን አሁን እንኳን ደስ አለህ ልትለኝ ትችላለህ ወንድሜ፡፡ ፍርዱ በመቅረቱ ደስታ ተሰምቶኝ አይምሰልህ፤ ህይወት ሁሌም ህይወት ናት። በውስጣችን እንጂ ከውጭ አይደለችም። ብዙ ሰዎች በአጠገቤ ይኖራሉ፤ እኔም በመካከላቸው ሰው እሆናለሁ። ልቤም አይደክምም ፈቃዴም በመከራ አይወድቅም። ይህም በእኔ የእምነት ህይወት ወይም የመኖር ግዴታዬ ነው።
ያን አደጋ ኖሬዋለሁ። ኖሬ የደረስኩትም ከስጋዬ ተቆርሶ ከደሜ የተቀዳ የጭንቅላቴ ቅሪት ነው። የቀረው ጭንቅላቴ የቀረው ማንነቴ ነው። ትዝታዬ መላህ ህይወቴ በዛ ተቆርጦ ተጥሏል። ደም እና ስጋ ያለሙሉ ጭንቅላት ባዶ ነው።
ታውቃለህ አሁንም ድረስ ልቤ አለ። ይህ ስጋና ደም መውደድ የሚችለው ስቃይ እና መሻት ተደምረው በልቤ ውስጥ ይኖራሉ። እናም ህይወት እንደዚህ መሆኑን አትርሳ። ዛሬም ፀዐይን እያየሁ ትንሽ ፈገግ ማለት እችላለሁ።
ሚስትህንና ልጆችህን ሳምልኝ፤ ሲረሱኝ አስታውሰኝ። አምናለሁ አንድ ቀን ያገናኘናል። ወንድሜ ሆይ ለራስህና ለልጆችህ እንድትጠነቀቅ በጸጥታና በንቃት እንድትኖር የልጆችህን የወደፊት ህይወት እንድታስብ እመክርሃለሁ። ቀና ህይወት ኑር።
እንደዛሬ የመንፈሳዊ ህይወት ጥልቀት በአካል ተሰምቶኝ አያውቅም። አሞኛል ግን እኖረው ዘንድ የግድ ነው። ከህይወት ብዙ ነገር አስቀርቻለሁ። ዛሬ ላይ በአለም የሚያስፈራኝ ነገር አለ፤ ቢሆንም የመጨረሻ የመጻፍ እድሌን ጽፊያለሁ። ያልረሱኝ እጆችህን ለመሳም ያብቃኝ።
ለወንድሞቼና ለእህቶቼ ደብዳቤ ፃፍላቸው በስሜም ጸሎት አድርግላቸው። በደስታም አውራቸው። ምናልባት እንገናኛለን። የእውነቴን ነው ወንድሜ ወደፊት ለሚገጥምህ ሁሉ ቸል አትበል። እራስህን ተንከባከብ። መኖር እና መኖር። አንድ ቀን ወጣትነታችንን፣ ያንን ወርቃማ ጊዜ፣ ያንን አፍላነት እንደገና ለመኖር ያበቃን ይሆናል።
እንደገና ለመጻፍ እስክሪብቶ በእጄ መያዝ መቻሌን አላውቅም። ግን ከአራት አመት በኋላ ወደ ጽሁፍ የምመለስ ይመስለኛል። እናም የምጽፈውን ሁሉ እልክልሃለሁ።
ኦ አምላኬ! ስንት ኖሬ የፈጠርኩት ነገር ሞቶ አይምሮዬ ውስጥ ተቀብሯል። የመከራ ቀስቴ የቀደደው ስጋ በደሜ ውስጥ ትርጉም የለሽነትን ፈጥሯል።
እሞታለሁ ብዬ ከምጽፍ አስራ አምስት አመት ከብዕሬ ብታገድ ይሻለኛል። ብዙ ጻፍልኝና ብዙ እውነታዎችን አስታውሰኝ፤ በእያንዳንዱ ንግግርህ ስለቤተሰብ በዝርዝርና በጥቂት ነገር ትዝ እንዲለኝ ጻፍልኝ።
ይህንን አትርሳ ንግግሮችህ ተስፋዬን እና ህይወቴን ያለመልማሉ። እስር ቤት እያለሁ በደረሱኝ ደብዳቤዎች ምን ያህል ሰላም ወደእኔ እንዳቀረብክልኝ ብታውቅ ኖሮ ባልዘገየህ ነበር። ያለፉት የመጨረሻ ሁለት ተኩል ወራት መጻፍም ሆነ መልዕክት እንዳላስተላልፍ መከልከሌ የከፋ ነው። እጅግ በጣም ታምሜ እራሱ ነበር።
እባክህ እንዳትተወኝ ከአራት አመት በኋላ ተመልሼ እመጣና አቅፍሃለሁ፡፡ ለሶስት ሩብ ሰዓታት በሞት ቅርበት ውስጥ ቆይቼ ያንን ረጅም ጊዜ ኖሬ የመጨረሻው የህይወት ሰዓት ቢደርስም ይኸው እንደገና በህይወት የመኖር እድል ተሰጥቶኛል፡፡
እናም አንድ ሰው በክፉ ካስታወሰኝ ወይም ከሰው ጋር ተጣልቼ ወይም አስቀይሜው ከሆነና ካገኛችሁት በደሌን እንዲረሳ ንገሩት። በማንም ላይ መራራ ቂም የለኝም፤ እናም እያንዳንዳችሁን ጓደኞቼን በዚህ ሰዓት ባቅፋችሁ ብዬ እመኛለሁ።
ዛሬ ውዶቼን ከመሞቴ በፊት ስሰናበት እረፍት ተሰማኝ። በዚህ ሰአት የሞት ዜናዬ ብትሰሙ እንደሚገድላችሁ አስባለሁ። ግን አሁን ማረፍ ትችላላችሁ ምክንያቱም እስካሁን በህይወት አለሁ፡፡
እና የምጠይቅ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ምን እያደረክ ነው? ዛሬ ምን እያሰብክ ነበር? ስለ እኔ የተሰማህ ነገር አለ? ዛሬስ እንዴት ነው አየሩ ብርድ ነው? ይህ ደብዳቤዬ ፈጥኖ ደርሶ እስከምታነበው እንዴት እንደጓጓው። መልዕክትህ እስኪደርሰኝ ቢያንስ አራት ወር ይፈጃል። ከ2 ወር በፊት የላክልኝን መልዕክት አየሁት፤ አድራሻዬ በደብዳቤህ ተጽፎ አለ። ደብዳቤውን ሳልከፍተው ገና እንዳየውት በጣም ነው ደስ ያለኝ።
ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበ ምን ያህል ጊዜ እንዳባከንኩ፣ ምን ያህል በህመም እንደተሰቃየሁ፣ ስንፍናና አለመኖር ተደምሮ ልቤንና አእምሮዬን እንደጎዳው ባስታወስኩ ቁጥር ልቤ ይደማል!። አዎን ህይወት ስጦታ ናት ደስታም ናት በእያንዳንዷ ቅጽበታዊ እድሜያችን የምንፈልገውን ማድረግ እንችላለን።
አሁን ህይወቴ እየተቀየረ ነው። እናም እንደገና በሌላ መልክ ተወልጃለሁ። ወንድሜ ቃል እገባልሃለሁ ተስፋ እንዳልቆርጥ ነፍሴን እና ልቤን በንፅህና አኖራለሁ። አዲሱ ልደቴ ካለፈው ዘመኔ የተሻለ ይሆናል ያ ሁሉ ተስፋዬ መፅናኛዬም ጭምር ነው።
የእስር ቤት ቆይታዬ ንጹህ ያልሆኑትን የስጋ ጥያቄዎቼን በሰውነቴ ውስጥ ገድሏቸዋል። ከዚህ በፊት ለራሴ የማላውቅ ሰው ነበርኩ። አሁን ግን መጉደል ዋጋ የለውምና የገንዘብ መከራ ይገድለኛል ብዬ አልፈራም።
ቻው ቻው ወንድሜ አጥብቄ እቅፍ አርጌ ለመሳም ያብቃኝ። እባክህ አትዘን ያለ ህመም በልብህ አስታውሰኝ። ምን እንደተፈጠረ በሚቀጥለው ደብዳቤ እነግርሃለሁ። እንግዲህ የነገርኩህን አስታውስ እያማረርህ አትኑር ሁልጊዜ ኑሮህን አደራጅ እድልህን አስተካክል ልጆችህን አስብ።
አሁን መጥተህ ባይህ ደስታዬን አልችለውም። ከምወደው ነገር ሁሉ ራሴን እያገለልኩ ነው። እናም ይህ መነጣጠል በጣም ያማል። ራሴን በግማሽ መቁረጥና ልቤን መቀደዴ በጣም ያቆስላል። ቻው ግን አይሃለው። አውቃለው አትቀየርም። እንደሁልጊዜው ውደደኝ። ትዝታህን እንዳታጠፋው በህይወት ውስጥ ውዱ ነገር ትዝታ ነው። ደህና ሁን። ቻው ሁላችሁንም።
| ለወንድሜ
ከዶስቶይቭስኪ |
(ፊዮዶር ዶስቶይቭስኪ ለወንድሙ ሚካኤል ዶስቶይቭስኪ ደብዳቤ ወደ ፒተርስበርግ ካስትል ዲሴምበር 22 በ1849 ዓ.ም)
ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
t.me/danelroza
ለፌስቡክ
👇👇👇
Fb.com/danelroza
ለሊንክደን ፡
👇👇👇
linkedin.com/in/danelroz
