10 Apr 2026, Fri

ልጄ ሆይ ! ሰውና ጥላ አንድ ናቸው ፤

በአንድ ወቅት በሀብቱ ግርማ ሞገስ የተጎናጸፈ፣ “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” ብሎ የሚያምን አንድ ባለጸጋ ነበር። የቤቱ ደጃፍ እንደ ንብ ቀፎ በሰው ይሞላል፤ በሄደበት ሁሉ የክብር ምንጣፍ ይነጠፍለታል። እርሱም እንዲህ ይል ነበር ፦ “እነዚህ ሁሉ ዘመድና ወዳጆች አሉኝ፣ ይሄ ሁሉ ሀብት አለኝ፤ ምን ያንሰኛል?” መመኪያውን በኪሱ እና በሰው ትከሻ ላይ አደረገ።

አንድ ክፉ ቀን መጣና አውሎ ንፋስ ሀብቱን ጠራርጎ ወሰደው። ያ በሰው የተሞላው ግቢው በአንድ ጀምበር ጭር አለ። መጀመሪያ “ክቡር ሆይ” የሚሉ አሽቃባጮች ጠፉ፤ ቀጥሎም “ወንድሜ” የሚሉ የቅርብ ወዳጆቹ ስልካቸውን ዘጉ።

አንድ ቀን በጣም ተቸግሮ፣ በሀብቱ ጊዜ ውለታ ለዋለለት የቅርብ ዘመዱ ደጃፍ ቆመ። ዘመዱ ግን በበሩ ቀዳዳ ተመልክቶት “የለም በሉልኝ” ሲል ሰማው። ባለጸጋው በድንጋጤ ደነዘዘ። ጎዳና ላይ ወድቆ ሳለ ፣ አንድ ሽማግሌ በአጠገቡ ሲያልፉ አዩትና ትከሻውን ነክተው እንዲህ አሉት፦

“ልጄ ሆይ! ሰውና ጥላ አንድ ናቸው። ብርሃን ሲኖር ይከተሉሃል፣ ጨለማ ሲመጣ ግን ጥለውህ ይፈረጥጣሉ። በሰው ተደግፈህ አትቁም — ሰው ታካች ነውና ሲሰለቸው ይጥልሃል። በሀብትህ አትመካ — ሀብት እንደ ደመና ነው፣ ይበተናል። “ሽማግሌው ቀጠሉ ፦ “ሁልጊዜም ቢሆን መደገፍ ያለብህ ፈጣሪ ላይ ነው። እርሱ ሲሰጡት የማይሰለች ፣ ሲለምኑት የማይቆጣ፣ ክፉ ቀን ሲመጣ ደግሞ ይበልጥ የሚቀርብህ ብቸኛ ኃይል ነው። የሰው እጅ ሰጥቶ ይነሳል ፤ የፈጣሪ እጅ ግን አንስቶ ያቆማል።”

ሰውየው በዚያች ቅጽበት የእንባ ዘለላዎቹን እየጠረገ ወደ ሰማይ አየ። ለካስ እስካሁን ተደግፎ የነበረው በፈራረሰ ግንብ ላይ ነበር። ዛሬ ግን በማይናወጠው ዓለት (በፈጣሪ) ላይ ተደገፈ።

የዛሬው መልዕክት ፦

በጉልበትህ አትመካ — ይዝላል !

በስልጣንህ አትመካ — ይሻራል !

በዘመድህ አትመካ — ይሰለችሃል !

ሁሉንም ስጥቶህ የማያመጻድቀው፣ ወድቀህ የማይንቅህና ሁልጊዜም “አለሁልህ” የሚልህ ፈጣሪ ላይ ብቻ ተደገፍ።

መልካም ቀን

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
http://t.me/danelroza
ለፌስቡክ 
👇👇👇
http://fb.com/danelroza
ለሊንክደን ፡
👇👇👇
linkedin.com/in/danelrozlroza

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *