10 Apr 2026, Fri

✴️ በፍቅርህ ተገለጥክልኝ ! ፤

በአለም ዳከርኩ፣ ዋተትኩኝ፣ ፍላጎቴን ፍለጋ ባዘንኩ ፣ እላይ እታች አለኩ ፣ ሮጥኩኝ ፣ ሮጥኩኝ የምይዘው ፣ የምጨብጠው ግን አጣው። ያየውት ሁሉ ሲያምረኝ፣ የተነገረው ሁሉ ሲያስደነግጠኝ፣ የሚባለው ሁሉ ስለእኔ እየመሰለኝ፣ ያወኩት ሁሉ ጥሎኝ የሚሔድ እየመሰለኝ እንዲሁ መረጋጋት ተስኖኝ፣ ስክነት ርቆኝ እንዲሁ ስብከነከን ኖርኩኝ።

መንፈሴ ሲደነግጥ ፣ ውስጤ ሰላም ሲያጣ ፣ ኮሽታው ሲያውከው ፣ ኡኡታው ሲያስደነብረው ከረመ አሁን ግን ነፍሴ የምርም አንተን ፈለገች፣ አንተን ናፈቀች፣ እቅፍህን አብዝታ ተመኘች። አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ተለመነኝ ፣ አንተ ታደገኝ ፣ አንተ ልቤን መልስልኝ ፣ ከአለሙ ውዥንብር አንተ በእቅፍህ ከልለኝ፤ በቤትህ አቆየኝ፤ በጉያህ ሸሽገኝ።

✅ አዎ ! አለምን አሰስኩ፣ ከአለም ጠበኩ፣ ከሰው ናፈኩ ነገር ግን አንዳች የሚገዛኝ አላገኘሁም ፤ አንዳች ቀልቤን የሚመልስልኝ ፣ መረጋጋትን የሚያድለኝ፣ ሰላምን የሚሰጠኝ፣ በፅኑ ተስፋ የሚሞላኝ አላገኘሁም። በመጨረሻም እንደ ደጉ አባቴ አብረሃም አንተን አጥብቄ ፈለኩህ ፣ በልቤ ውስጥ ሆነህ ባላይህም፣ ከማንነቴ ተዋህደህ ባላገኝህም፣ እነሆ አሁን በፍቅርህ ተገለጥክልኝ ፤ በመውደድህ ጥግ አወኩህ ፣ በበረከትህ ልኬት ፣ በስጦታህ ብዛት በግልፅ ታየሀኝ። እወድሃለሁ እያለኩ መውደዴን በተግባር ባልገልፀው ፣ በፈለኩት ልክ ለቃልህ ባልገዛ ፣ ትዕዛዛትህን ባላከብር ፣ እንደ ፍቃድህ ባልኖር ላንተ ያለኝን ፍቅር ግን አንተ ታውቃለህና አንተው ተረዳኝ። ልቤን በምታውቀው ፣ ውስጤን በተረዳሀው ልክ ነፍሴን ከመጥፋት ታደጋት፤ ህይወቴን ከብክነት ጠብቃት፤ ከማንም በላይ የሚሆንላት ድንቅ የዘላለም አባት እንዳላት ትመሰክር ዘንድ ብርታቱን አድላት።”

✅ አዎ! ወዳጄ..! ከአምላክህ ጋር እንዲህ ተነጋገር። ይጎበኝህ ፣ ይቀድስህ ፣ ይባርክህ ዘንድ መንገዱን ክፈትለት። እርሱ በሚፈልግህ ልክ ባትፈልገው እንኳን እንዲያገኝህ ግልፅ ቦታ ተገኝለት። ትቢያ ውስጥ ብትደበቅ ፣ በዓለም ብትዋጥ ፣ ሱስ ውስጥ ብትሸሸግ፣ ከእውቀትህ ብዛት ብትሰወር ፣ በፍልስፍናህ ጣሪያን ብትነካ ፣ በልብህ ልትክደው ብትሞክር ፣ በቃላትህ ብታብጠለጥለው ፣ ስለመኖሩ ብታንገራግር እርሱ ግን በዝምታ ውስጥ ያይሃል ፤ ይሰማሃል ፤ መንገድ የጠፋበት ፣ ጨለማ የወረሰው ልጁ ነህና ብታጠፋም ፣ ብትበድለውም ፣ ስሙን ብታጠለሸውም ጆሮ ሰጥቶ ይሰማሃል፤ ከልቡም ያዳምጥሃል። መሔጃ የሌለህ ቢመስልህ እንኳን ዘላለም በእቅፉ ማኖርን የሚወድ አምላክ እንዳለህ አስታውስ፤ ሰሚ ጆሮ ያጣህ፣ ትኩረት ሰጪ ልብ የተነፈክ፣ ተመልካች አይንም ያላገኘህ ቢመስልህ ሁሌም በትኩረት የሚመለከትህ፣ ቃልህን የሚሰማህ ድንቅ አምላክ እንዳለህ እመን። በአለም ዓይን እራስህን መለካትህን አቁም፤ በአምላክህ ግሩም ስጦታዎች እራስህን ቃኝ። 🌘🌒💫✨

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
http://t.me/danelroza
ለፌስቡክ 
👇👇👇
http://fb.com/danelroza
ለሊንክደን ፡
👇👇👇
linkedin.com/in/danelrozlroza

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *