10 Apr 2026, Fri

ቪንሰት ቫን ጎግ አለም ላይ እስከዛሬ ከተፈጠሩ የስነጥበብ ባለሙያዎች ለየት ያለ ስብዕና የነበረው ሰው ነበር። በግዜው የእሱን የስዕል አቅም ያልተረዱ ሰዎች ከአንድ ቀለም ደፊ በቀር አስበውት አያውቁም።

የቫንጎግ ሥዕሎች ከመቼውም ጊዜ የላቀና የሚወደድ እንደሚሆን በግዜው ማንም ሰው አልተረዳም ነበር። ሆላንዳዊው አርቲስት ቫን ጎግ በህይወት ዘመኑ ሁሉ በድህነት ውስጥ ስለኖረ በክረምት አንዳንድ ሥዕሎቹን እንዳይበርደው ያቃጥላቸው እንደነበር ቅርቡ ያሉ ሰዎች ይናገራሉ።

በሕይወቱ ውስጥ አንድ ሥዕል ብቻ «Red grape vegetable» በ400 የስዊዝ ፍራንክ ለመሸጥ ችሏል። ነገር ግን በድህነት አሳሩን በልቶ ከሞተ በኋላ ከ900 በላይ ሥዕሎችን እና የጥበብ ሥራዎችን ትቶ ነበር ያለፈው።

በህይወት ሳለ በከፍተኛ የአዕምሮ ችግርና በመጣል በሽታ ይሰቃይ እንደነበር የታሪክ መዛግብቱ ይናገራል። ለእለት ጉርሱ የሚሆን አንድም ዳቦ ማግኘት የማይችል ምስኪንና ዝምተኛ ሰውም ነበር። አዎ ዓለም እናንተን እየከፈላችሁት ያለውን ዋጋ በጣም ዘግይታም ቢሆን ልትረዳ ትችላለች። ያኔ ግን እናንተ ላትኖሩ ትችሉ ይሆናል።

እስቲ ዛሬ ቪንሰንት ቫን ጎግ ለወንድሙ ቴዎ ከላከው ደብዳቤ ውስጥ አንደኛውን ላካፍላችሁ፦ 📃

( ..ውድ ቴዎ.. 🎴 )

ኑሮ እንዴት እየሄደ ነው? በነገሮች ላይ ያለንን ደስታ በማሳጣት ወደ ድብርት ከመምራት ውጭ አዕምሮ ሌላ ምን ስራ አለው?። ብሩሽና ቀለሜ ሳያረጅ እኔ ቀድሜ እያረጀው ነው። ነገሮችን በድጋሚ ብገነባም ጊዜ አጎንብሶ ሁሉም ነገር ይፈራርሳል። ምን ላድርግ? ዓይኖቼ ከለመዳቸው ውጪ አዲስ መስመሮችና ቀለሞችን የመፍጠር ፍላጎቴ እለት’ለት እየጨመረ ነው።

የድሮ ቀለማት በጠቅላላ ልቤ ውስጥ አሳዛኝ ጭላንጭል አላቸው። በተፈጥሮ ነው ወይስ አይኔን አሞኛል?፤ ሁሌ በውስጤ የተገገረውን ቅዝቃዜ ለማሞቅ የማይጠቅመኝን እሳት እንዳራገብኩ ነው!።

በሀዘንተኛ ልቤ ውስጥ የደስታ መስመሮች አሉ። ቀለሞቼ በወፍ እና በስንዴ መሃከል እንዳለ አንገት ይመሰላል። ለምፈልገው ሳይሆን ለሚያስፈልገኝ ነገር ጎንበስ እንደማለት ያለህ። ገበሬው ከጫማው ላይ ያለን አቧራ እንደሚያራግፍ እኔም መከራዬን ከላዬ ላይ ባራግፍ ብዬ እመኛለሁ። ሙሉ ለሙሉ ባይለቅም የተወሰነ ደስታ እንዳለው ግን አውቃለሁ። አስቀያሚ ነገር በሚያምር ነገር ውስጥ ልናገኘው የምንችለው የጥበብ ባህሪ ነው። የአርቲስት ዓይን ደግሞ ያ አያመልጠውም።

ይገርምሃል ዛሬ የራሴን ምስል ሳልኩኝ። እና ሁሌም ጠዋት ጠዋት መስታወት ሳይ ለራሴ እንዲህ እለዋለሁ፦“አንተ ቀጭን ፊት፣ አንተ አስቀያሚ ቪንሰንት ፊት፣ ለምንድነው ደስተኛ መሆን ያልቻልከው?” ስጨርስ መስታወቱ ላይ ተፍቼ እወጣለሁ። አዎ ዛሬ ፊቴን ተፈጥሮ እንደፈለገችው ሳይሆን እኔ እንደምፈልገው እንዲሆን ቀየርኩት። ሁለቱ አይኖቼን እንደ ተኩላ ቆራጥነት እንዲኖራቸው አረንጓዴ ቀባዋቸው፤ ፊቴን እሳት የመሰለ ፂም ዙርያውን ለወስኩት። በስዕሉ ውስጥ ጆሮዬ ወደላይ ወጥቷል። ማስተካከል አላስፈለገኝም። የተላጨ ስል ብሩሼን እንዳነሳሁ የቀባባሁት ማንነቴ ግልጽ እይታ አይደለም ነገሩ ድብልቅልቅ ያለ ነው። ጭንቅላቴ በስዕሉ ጠረዝ እንደወጣና እንደገባ በመሃከል ያልቃል። እንግዲህ ያንን ትርፍ የስጋ ቁራጭ ምን ላደርገው ነው?። ልኬን ለማታውቅ እና የወደድኳት ለመሰላት ሴት ላድርገው?። ችግር የለውም ጥቅሙ አንድ ላይ ነው። ይኸው ጆሮዬ ያቺን ነገረኛ ሴት ይናገራታል። አሁንማ በጣቴ መስማትም ማየትም እችላለሁ። ከአምስቱ በላይ ስድስተኛው የስሜት ህዋሴ የብሩሽ እና የጣት ጥምረት ከዚህም በላይ ያደረጋል። የስዕሉ ሸራ ላይ ህይወት ይፈጥራል፣ ያስቀዋል፣ ያናደዋል ከፈለገም ሸራውን ያቃጥለዋል።

ሁሌም ብቻዬን ተቀምጬ አሰላስላለሁ። አዎን አለም ዥንጉርጉርነቷ አስረጅቷታል። የስዕሉ ገጽታ ይበልጥ ሀዘን ፈጠረብኝ። የመንፈስ ጭንቀቴ ገዝፎና ወድቆ እንዳይጨፈልቀኝ ሰጋሁ። ብሩሽ፣ ቀለሞች እና የእኔ ፍጥነት፣ ቀጥ ያለ እና አጭር ቅብ፣ ስል እና ግርማ ሞገሳም ቀለሞቼ ግልጽ እና ጥንታዊ ናቸው። ቀይ፣ ቢጫና ሰማያዊ ዓለም ከመጀመሪያው የጠፈር እንቁላል ላይ የተፈለፈ ይመስል ነገሮችን ወደ ድንገተኛ ፍንዳታ እንዲቀይራቸው እፈልጋለሁ፡፡

አሁንም ድረስ አስታውሳለሁ። ሊመሽ ሲል ወይም ከመንጋቱ በፊት የፀዐይ አድማስ ሰማዩን በቀይ ቀለሙ ያረጥባል። የዱር ፍራፍሬዎችን ለመስረቅ እየሄድን ነበር። ስንደርስ ዛፉ ላይ ወጣው። ትንሽ ቆይቶ ከዛፉ ጫፍ ላይ ነጠብጣብ አረንጓዴ ያለባት ቢጫ ወፍ እያየሁ መመሰጥ ጀመርኩ። በጣም ትንሿ ወፍ በቅርንጫፎቹ መካከል በደስታ ስትዘልል በድንገት ሚዛኗ ስታ በላዬ ላይ ታርፋለች፤ በደረቴ ጫፍ ላይ ማረፏን ስታውቅ በድንጋጤ የተጣመመ አንገቷን እየገፋች በርራ ለማምለጥ ትወራጫለች። ከትንሽ የትግል ደቂቃ በኋላ የተንጋለለ አንገቷን እንደተሸከመች ተሰናበተችኝ። አስታውሳለሁ ያንግዜ ዐሥራ ሁለት አመቴ ነበር። እናም በነጭ ሸሚዜ ላይ ትታኝ ስለሄደችው ወፍ ለረጅም ግዜ አስቢያለሁ። በንጹህ ሸሚዜ ውስጥ ስትርመሰመስ ደረቴ ቢከፈት በደስታ ከበሮ እየመታ በታየ ነበር። ብቻ ሀሳቡ ብዙ ነው ይቅርብኝ።

እንዲህ ያለህ ነው በስንዴ ማሳ ውስጥ ተደብቄ ቢጫ ቀለም ከሰማዩ ተጋድሞ አያለሁ። የዚህች ብሩህ ፕላኔት ጨረር ላይ አፈጣለሁ፤ የአለም መንፈስ ባለበት ሁሉ የፀዐይ ብርሃን የዓይኔን ብሌን እስከሚያቀልጠው ድረስ ያለማቋረጥ እመለከተዋለሁ። ሁለት ነገሮች ነፍሴን ያንቀሳቅሳሉ። ፀዐይን ማየት እና ሞት። በከዋክብት መሃከል መጓዝ ያምረኛል። አውቃለሁ ይህ ምስኪን ሰውነቴ ወደኋላ አስቀርቶኛል!። መቼ ይሆን የምድር ሰዎች በጠቅላላ ያፈሰስነውን ደም በመሃረባችን እየጠረግን ከዚህ ስፍራ የምንሄደው? ብንችልስ ወዴት እንሄዳለን? ወደ እውነተኛው ህልማችን?።

ትላንትና እራሴን በስንዴ ማሳ ውስጥ አስገብቼ አበባ የተቀመጠበትን ሸክላ ባረጀ ብሩሽ ቀባሁት። እንዲህ ሳደርግ ቢጫ እና ቀይ ወጋገን ከጭንቅላቴ ላይ አየር አልባ ሆኖ እንደ ወፍ ትዝታ ያበራል። አዎን ወፎች ያለዓየር እንደማይበሩት፤ ዓሳዎችም ያለ ውሃ እንደማይኖሩት ሁሉ እኔም ያለስቃይ እንዲያ ነኝ። የስንዴ ጥሬ እና የወፍ ድምፅ፤ በድጋሚ ስንዴ እና ወፍ ይህ ጭንቅላቴ ውስጥ ደጋግሞ እያስተጋባ ነው። ሁሉም ነገር ህልም ነው። የህልም ከንቱነት እና ያረጀ ብሩሽነት በጊዜ የመታላለችን ምስል ነው። ነገር ግን በቅርቡ አቧራኔን አጸዳለሁ። እና ወፏን ከደረቴ ወደ ፀሐይ እለቃታለሁ። አዎ በዚህ መሳርያ ሰይፍ እታጠቃለሁ!፡፡

የእኔ እውነት በእሳት ላይ እንዳለ እንጨት እየነደደች ነው። እንደ ነጭ እና ጥቁር ህይወት ግራጫ ናት። ግራጫማነቷም ማለቂያ የሌለው እድለቢስነት እንደተሸከመ ይኖራል። ግራጫ ቀይ ነው፣ ግራጫ ሰማያዊ ነው፣ ግራጫ አረንጓዴ ነው። ትምባሆ ይነዳል ህይወትም እየፈሰሰች ነው። ግራጫ መራራ ጣዕም አለው ብዙ ጊዜ ባለማወቅ እንቀላቅለዋለን ነገር ግን ትንሽ ቆይተን እንፀፀታለን። ልክ እንደ ህይወት እድሜያችን በጨመረ ቁጥር ነጋችን ከእሱ ጋር ይጣበቃል። ለዚህ ነው ከፍታ ላይ ትቻት የምሄደው፡፡ ግን ለምን ይመስልሃል? እንደገና ትወድቃለች እንደገና ትሰበራለች መከራ እስከ እድሜዋ ድረስ አያልቅም!። ቻው ቲዮ ወደ ጸደይ እየሄድኩ ነው..።

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
http://t.me/danelroza
ለፌስቡክ 
👇👇👇
http://fb.com/danelroza
ለሊንክደን ፡
👇👇👇
linkedin.com/in/danelrozlroza

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *