መጀመሪያ ላይ ሰዎችን መታገስ እችላለሁ ብዬ አስብ ነበር፤ የውሸት ሳቃቸውን፣ ትርጉም አልባ ቃላቸውን፣ ብዙ እርቀት ሳይጓዝ የሚፈርሰው ቃልክዲናቸውን መታገስ እችላለሁ ብዬ አስብ ነበር። ቢሆንም ከግዜያት በኋላ ከእነሱ ጋር ያለኝ እያንዳንዱ ግንኙነቴ እና ውይይቴ ከነፍሴ አንዳች ነገሬን እያጎደለ እንደሆነ ተሰማኝ። በርግጥ ይህ አመላቸውን ችዬ ለመኖር ሞክሬያለሁ። ከእነርሱ ጋር መሳቅ፣ ቀናትን መጋራት፤ ነገር ግን ሁልጊዜ የራሴ ያልሆነ ሕይወት እንደምኖር፣ የእኔ ያልሆነ አየር እንደምተነፍስ፣ እኔ የማልሰማቸውን ቃላት እንደምናገር ተረዳሁ።
ከዛ.. አንድ ቀን ግን እርቄ ለመሄድ ወሰንኩ፤ አዎ መምረጥ እንዳለብኝ ተሰማኝ፤ እኔን ወይም እነሱን፤ እለት’ለት ከመቁሰል ፈንታ ብቸኝነትን፣ ከድምፅ እና ረብሻ ፈንታ ጸጥታን፣ ከሌሎች ይልቅ ራሴን!። በመጀመሪያ ከባድ ነበር፤ ይናፍቁኝ ጀመር ድምፃቸውን ናፈቀኝ፣ ወሬያቸው ናፈቀኝ፤ ነገር ግን ከጥቂት ወራት በኋላ ራሴን መስማት ጀመርሁ፤ ራሴን መረዳት ጀመርሁ። በዚያች ትንሽ ክፍሌ ውስጥ ጸጥ ያሉ ግድግዳዎች መካከል ያልነበረኝን እውነት ተቀምጦ አገኙሁት።
እዚህ ማንም አይመጣም ሊዋሸኝ ወይም እኔ ያልሆንኩትን ምስል ሊፈጥርብኝ አይቻለውም። መገለል መሸሽ አይደለም፤ ፈጽሞ መሸሽ አልነበረም። መገለል ወደ ነፍስ ውስጥ የሚገባ ጥልቅ ግልጸኝነት ነው። ዓለም በጨካኝነት ብትቀረጥፈኝም ከቀረኝ ቅንጥብጣቢ ውስጥ ከነፍሴ ጋር ታማኝ ለመሆን የሚሰጥ እድል ፈንታ ተጋራሁ። ልቤን አዳምጣለሁ፣ ፍላጎቴን አስተውላለሁ፣ ፍርሃቴን አሸተዋለሁ፣ በፊት በሰዎች መካከል ያደረግኩት አሳፋሪነትን ቁጭ ብዬ እታዘባለሁ።
ከእንግዲ መልሳቸውን፣ ምክራቸውን፣ ሐሰተኛ ተስፋቸውን አልፈልግም። ከእነርሱ ጋር ያለው ሕይወት እንደ ተባይ በልብስ ላይ ፈልቶ ሳንባን ይሞላል፤ ከዛ ምንም የለም ጸጥ ያለ ጉዳት ብቻ ይቀረናል። ዛሬ ላይ ግን ብቻዬን ሆኜ በነፃነት መተንፈስ እችላለሁ። በጸጥታ መጓዝ እችላለሁ፤ ከፍርሃት ተለይቼ መጻፍ እችላለሁ፤ ያለ ገደብ ማሰብ እችላለሁ፤ ብቸኝነት ከባድ ነው ግን እውነተኛ ነው። ከማንኛውም ሐሰተኛ ሳቅ ይልቅ እውነተኛ ለቅሶ ትርጉም አለው። ከማንኛውም የማይጨበጥ ተስፋ ይልቅ ተስፋ መቁረጥ እረፍት አለው። እያንዳንዱን ቀን ባለፍኩ ቁጥር ስለራሴ አዲስ ነገር እማራለሁ። በዚያ ሁሉ ረብሻ መካከል መማር ያልቻልኩትን ሁሉ እገነዛበለሁ።
በመጨረሻም ይህን ተረዳሁ ከሰዎች መራቄ ኪሳራ አልነበረም ይልቅስ ግኝት ነበር። እውነተኛው ዓለም በሌሎች መካከል የሚያበራ የውሸት ፀዐይ ሳይሆን በውስጤ የተለኮሰች አንዲት ሻማ ነች። በዚህ ጸጥታ፣ በዚህ እንግዳ ነጻነት ውስጥ ጨካኝ ነገር ግን እውነተኛ መሆን ምንኛ ደስ ይላል!።
ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
http://t.me/danelroza
ለፌስቡክ
👇👇👇
http://fb.com/danelroza
ለሊንክደን ፡
👇👇👇
linkedin.com/in/danelrozlroza
