12 Dec 2025, Fri

የለውጥ ፍርሃት – Metathesiophobia

ሰው በተፈጥሮው አንድ አይነት ዑደትን የመውደድ ባህሪይ አለው ፤ ጠዋት ፀሐይ ትወጣለች ፣ ማታ ደግሞ ትጠልቃለች ፣ በዓመት አንዴ የዝናብ {ክረምት} ወቅት ይመጣል ከዚያም ይሄዳል … አንድ ዓይነትነት !

እነዚህ የለመድናቸው ሁኔታዎች ለወጥ ሲሉ ግር ይለናል ፤ ይህ ስሜት ደግሞ በትክክለኛው መጠን መኖሩ የጤናማነት ምልክት ነው ፤ ነገር ግን ምንም ዓይነት ለውጥን ፈጽሞ የማንፈልግ ከሆነ የ“ፎቢያ” ችግር ሊኖርብህ ይችላል፡፡

የለውጥ “ፎቢያ”የአንድን ሰው የመኖር ጉጉት የሚሰርቅ የፍርሃት አይነት ነው ፤ የዚህ ፍርሃት ተጠቂዎች በኑሮ ደረጃቸው ፣ በእውቀት አለማቸው ፣ በንግዱና በስራ መስካቸውም ሆነ የሚኖሩበትን ስፍራና ሁኔታ አስመልክቶ ምንም ዓይነት ለውጥ የማድረግ ፍላጎቱም የላቸው ፤ ከመጣም ለውጡን አጥብቀው ይቋቋሙታል፡፡

በአጭሩ ምንም ዓይነት ነገር ከቁጥጥራቸው ውጪ እንዲሆን ስለማይፈልጉና ለውጥ ደግሞ ያንን ሁኔታ እንደሚፈጥርባቸው በማሰብ ስለሚፈሩ ባሉበት ሁኔታ ኖሮ ማለፍን ይመርጣሉ፡፡

ዙሪያችን ተለውጦ ሳለ አለመለወጥ ፣ የእድገት እድል እያለ እንኳን መኖሪያን ፣ ስራንና የንግድ ዘርፍን መቀየር መፍራት ፣ ለማደግ አለመፈለግና የመሳሰሉት ጠንቆች የዚህ ፍርሃት ሰለባዎች ችግር ናቸው፡፡

ለማስታወስ ያህል …

• ለውጥን በጥንቃቄ አይን ማየትህ ትክክለኛ የለውጥ ምላሽ መሆኑን አስታውስ፡፡

• ወደድክም ጠላህም ለውጥ የሕይወትህ አካል መሆኑን አምነህ ተቀበለው፡፡

• አንተ የለውጥ እርምጃ ወሰድምክ አልወሰድክ ፣ ለውጥ መምጣቱ አይቀርም፡፡

• ለውጥ በራሱ ሲመጣም ሆነ፣ ለውጥ በአንተ አነሳሽነት ሲከናወን ከለውጡ ጋር አብረህ መራመድ ለስኬታማነትህ ወሳኝ ነው፡፡

• ከለውጥ ጋር የሚመጣ የማይመች ስሜት ጤናማ ፣ ትክክለኛና ሁሉም ሰው የሚጋራው ስሜት መሆኑን አትርሳ፡፡

ራዕያችሁን ማወቅና ያንን መከተል ነባሩን አሰልቺ ሂደት በመቀየር ወደ አዲስ ለውጥ የሚያሸጋግር አስገራሚ ልምምድ ነው፡፡

ራሳችንን እንፈትሽ ፡ ራሳችንን እንመልከት።

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም t.me/danelroza

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *