12 Apr 2026, Sun

የሁልጊዜ ጥያቄዬ ይህ ነው ፤

ለምንድን ነው ከብልህ ሰዎች ይልቅ ደደብ ሰዎች በሶሻል ሚድያ እውቅና የሚያገኙት?። ታድያ አንድ ልክ የሆነ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። አንድ ሰው ልክ የሚለው ነገር ባይኖረውም ልክ የሆኑ ነገሮች Evidence or Factን ይቀበላል።

በመጀመርያ ደረጃ ይህ ጥያቄ ከብልህነት ይልቅ የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀምን ከማወቅ የሚመጣ ነው። በአጭሩ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው፦

(ሶሻል ሚዲያ ትኩረትን እንጂ ጥበብን አይሸጥም)

የሶሻል ሚድያ ፕላትፎርም በታየልን ልክ ያሳየናል። አንድ ሰው ለማየት ግዜ የሚወስድበት በጠቅላላ ትኩረት የሚስበውን ነገር ነው። ስለዚህ ብዙ ሰዎች ትኩረታቸውን የወሰደ ጽሁፍም ሆነ ቪድዮ ላይ በቆዩ ቁጥር View እየቆጠረ ይመጣል። በትንሹ አልጎርይዝሞቹ የሚያበረታቱት እነዚህ ናቸው፦

1.የሚያስቆጣቸውን

2.የሚያሳዝናቸውን

3.ልቀኝነት/መረንነት

ባጭሩ ቀላል እና ፈጣን ነገሮች በማኀበረሰቡ ተመራጭ ናቸው። ጥልቅ ሐሳብ ደግሞ ጊዜ ሰጥቶ የማሰብ ቆይታን ይፈልጋል፤ ያን መጨናነቅ ደግሞ ማንም አይወድም።

(“ደደብነት” ቀላል ነው፤ ብልህነት ግን ያደክማል)

ለምሳሌ ብልህ ሰው ሲናገር ለመስማት መመሰጥ፣ ከሌላ ግዜ በተለየ መልኩ ማሰላሰል እና ብዙ ጥያቄዎችን እራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ስለዚህ ብልህ ሰዎች ሲያወሩ እያንዳንዷን ሰከንድ መከታተል፣ ንግግሩን መረዳት ግድ ይላል። ደደብ ሰው ሲያወራ ግን ግን ምንም ነገር አያሳልፈልግም፤ ጆሮ እና ዓይን በቂ ነው።

(አብዛኛው ሰው እሱን የሚመስለውን ሰው ይወዳል)

ማኀበረሰቡ ከራሳቸው ጋር የማይገናኝ የሚመስላቸውን በጠቅላላ አይወዱም። የተለመደ ነገር ያስደስታቸዋል። አንድ ሰው በተፈጥሮ ሊረዳ የማይችለውን ነገር አይወድም፤ የማይወደውን ደግሞ አያይም። የማይወደውን አያይም ስል የሚጠላውን ነገር አይመለከትም ማለቴ አይደለም። እንደውም የሚጠላው እና የሚያናደው ነገር ላይ ትኩረት ይሰጣል። ቢሆንም ግን የማይገባው ብቻ ሳይሆን የሚጠላው ጭምር ሲሆን ሊሰማው ሆነ ሊመለከተው አይፈቅድም። ስለዚህ የሚፈትናቸውን ሰዎች ለመራቅ ወደኋላ አይሉም። “ቀላል እና አስቂኝ” ሰው በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ይሆናል።

(ትኩረት እና ገንዘብ)

ጥንት የነበሩት ማኀበረሰቦች የሚገዙት አንድ ትልቅ የሆነ የትኩረት ማዕከል ነበራቸው፤ እሱም ጥበብ ነው። ጥበበኞች ከነገስታቶች አማካሪነት፣ ከስዕል እና ዘፈን ጀምሮ የሃይማኖት መምህርነት ተፈላጊነት የነበራቸው ሙያ ነበሩ። በዛን ግዜ ጥበበኛ ወይም አዋቂ ሰው ይሰማል ይከበርማል። ከዛ በDark age ግዜ ደግሞ ኢንዱስትሪያሊዝም መጣ። ከእጅ ሙያ ጀምሮ የማሽን ቴክኖሎጂን መስራት የሚችሉ ተፈላጊ የመሆን እድል ነበራቸው። ዛሬ ላይ በAI ዘመን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ወደመሆን ደርሷል። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ህይወት ለማቅለል ያመጣቸው ቴክኖሎጂዎች የሰው ልጅን ቅሌት የሚያበረታታ ነቀርሳም ጭምር ነው። በአሁን ዘመን ገንዘብ ትኩረት ነው። ብዙ ትኩረት ደግሞ የሚገኘው ከሶሻል ሚድያ ነው። ሶሻል ሚዲያ የሚገዛው ነገር ሃሳብ ሳይሆን እይታ view ነው።

(ብልህ ሰዎች ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ አይደሉም፤ ወይ ዘግይተዋል ወይ እጅጉን ፈጥነዋል)

ብልህ ሰዎች የገንዘብ ሳይሆን የሃሳብ ባለፀጋነትን ይሻሉ። አዳዲስ ፕላትፎርሞች መጡ ሲባል ቀድሞ ለመሞከር ጥርጣሬ ውስጥ ይገባሉ። ስለዚህ ሶሻል ሚድያው ጋር ለመቅረብ አንድ እርምጃ ወደኋላ ናቸው። ቢገቡና ቢጀምሩ እራሱ በዚህ ደናቁርት ማኀበረሰብ የሚወደድ አይሆንላቸውም። ምክንያቱም እውነት ያወራሉ እና ደግሞ አይዋሹም!። ለዛም ነው ዓለም ደደቦችን እያከበረች ሳይሆን ትኩረትን እየወደደች ነው የምላችሁ!። እስቲ የዚህ ሃሳብ ስንግ የሆኑ ፍልስፍናዎች አንስቼ አንድ ሁለት ልበላችሁ።

(ፍሪድሪክ ኒቼ –The Psychology of Herd ወይም የመንጋ ሥነ-ልቦና)

«መንጋዎች ሁሌም እንደዚህ ናቸው፤ ሰውን የሚከተሉት ከፊታቸው ስለሚሮጥ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም!»

ኒቼ የመንጋ ስነ ልቦና ብሎ ባነሳው ሃሳቡ ላይ ብዙሃኑ ሰዎች እውነትን ሳይሆን ከእነሱ የሚሄደውን ወይም የሚመስለውን እውነት አድርጎ የመቀበል Social behavior አላቸው ይለናል። መንጋው ፈታኝ ጥያቄ የሚያነሳበትን ሰው ይጠላል፤ ከዛ በተለየ እንዳያስብ የሚያዝናናውን አጥብቆ ይከተላል። ሶሻል ሚዲያ ይህን ተገን በማድረግ Herd Logic ውስጥ ያለን ሰው የበለጠ የመፈመሻ እድል ይከፍትለታል። ኒቼ ይህን በተመለከተ እንደህ ይላል፦«እውነት ለሰዎችን ምቾት አይሰጥም ቅዠት የበለጠ ዘና ያደርጋቸዋል»

(አርተር ሾፐንሃወር – The Emotions of society ወይም የማኅበረሰቡ ስሜት)

ሾፐንሃወር በዚህ ሃሳብ ላይ ያለውን አመለካከት ብጽፍ ሁለት ትልልቅ ምዕራፍ ይወጣዋል። ያን በሌላ ግዜ ከመፅሐፉ ክፍሎች ወስጄ አናላይቲክ አደርገዋለሁ። ሾፐን ሃወር ብዙሃኑ ሰዎች የሚመሩት በስሜት እንጂ በአእምሮዋቸው አይደለም ይለናል። ስሜት የሚሰጣቸውን ግዜ ሰጥተው ይከታተላሉ፤ እንዲያስቡ የሚያደርጋቸውን ግን ይርቃሉ። ስለዚህ ጩኸት ያለው ይዘት ይታያል፣ ጸጥ ያለ ጥበብ ግን ቀስ በቀስ ይጠፋል። እዚህ ጋር ሾፐንሃወር እንዲህ የምትል አባባል አለችው፦«ሰው የሚወደው ነገር ካለው እውነት ስለሆነ አይደለም ይልቅስ ስለሚያስደስተው ነው።»

ፍራንዝ ካፍካ – Empty Fame and Alienation ወይም በባዶ ዝና መሟትት እና መጥፋት)

ካፍካ የሰው ልጅ በማይመጥነው ስርዓት ውስጥ እየሟሟና እየጠፋ እንደሆነ ይነግረናል። ለዛም ነው ሰሻል ሚድያ ላይ የሚቀርብ ሰው ከትክክለኛ ማንነቱ ይልቅ አስመሳይነቱ የሚጎላው። ስለዚህ ባዶ ታዋቂነት ይበዛል፤ በተቃራኒው ትርጉም ያለው ነገር ቀስ በቀስ ይደበዝዛል። ካፍካ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦«ትርጉም የሌለው ታዋቂነት አዋቂነትን ያጠፋል!።»

የሦስቱን ሃሳብ በአጭሩ ስነግራችሁ ልክ እንደ ኒቼ «The actor» ወይም የመድረክ ሰው መሆን የበለጠ ታዋቂነትን ያተርፋል። ጥሩ ተናጋሪ ከጥሩ አሳቢ በላይ ቦታ ይሰጠዋል፤ መፅሐፉን ከጻፈው ይልቅ መፅሐፉን የሚተነትነው ሰውዬ የበለጠ እውቅናን ያገኛል። ኒቼ The actor በሚለው እሳቤው ላይ እንዲህ ይለናል፦«ብዙዎች የሚኖሩት እንደ ተዋናይ ነው፤ እንደ ሰው አይደለም።»

ሾፐንሃወር ደግሞ ዝናን ከሌላ ቦታ እንደመበደር ያየዋል። ዛሬ ብናገኘውም ነገ ደግሞ እናጣዋለን። ዛሬ ያጨበጨበልን እጅ ነገ በጥፊ ከማለት ወደኋላ አይልም። ለዚህ እሳቤው የሚሆን አባባል ጣል ላድርግላችሁ፦«ዝናን ማግኘት ቀላል ነው፤ አብሮን እንዲቆይ ማድረግ ግን ከባድ ነው!።»

ካፍካም viewer prison ወይም አይቶ የማመን እስረኝነት ብሎ ይገልጸዋል። ይሄም ሰው ዘወትር በሚያየው ነገር ውስጥ እንደሚኖር የሚገልጽ ነው። የማንመለከተው ነገር እንደሌለ ይቆጠራል። በካፍካ አባባል መርሐ-ጽሁፉን ልዝጋው፦«የሚታይ ሕይወት ብቻ ሲኖረን ሕይወታችን ትንሽ ትሆናለች።»

በመጨረሻም ዛሬ ላይ ጩኸት ቢያገዝፈንም ጸጥታ ግን ያኮስሰናል። የሚታይ ሰው ይከበራል የሚያስብ ሰው ግን ይወገራል!። ሶሻል ሚዲያ የሚያበረታተው ጥበብን ሳይሆን ቀላል ስሜትን ነው። ብልህ ሰው አይጮኽም፤ ስለዚህ አይታይም። እናም ማሰብ ይቀጥላል፤ ሃሳብም ያለሃሳብ ይኖራል።

ማርክ ትዌይን እንዲህ ይላል፦«ጩኸት ምንም ነገር አያረጋግጥም፤ ብዙ ጊዜ እንቁላል የምትጥል ዶሮ አስትሮይድ እንደያዘች ያህል ሰፈሩን በጩኸት ታናጋለች!።»

ይቀላቀሉ ለቴሌግራም
👇👇👇
http://t.me/danelroza
ለፌስቡክ 
👇👇👇
http://fb.com/danelroza
ለሊንክደን ፡
👇👇👇
linkedin.com/in/danelrozlroza

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *