ልጁ በአጋጣሚ ከቤት ወደ ደጅ ሊወጣ ተዘጋጅቶ ነበር። የቤቱን በር እንደተራመደ “ከዚህ ቤት ተባረሃል ! ተመልሰህ እንዳትመጣ !”
የሚል ሀይለ-ቃል ጆሮውን ጭው አደረገው። ለምን ? እንዴት ? ወዴት ? የሚል ጥያቄም ሆነ ክርክር ሊያቀርብ አልሞከረም። ቀጥሎም ትቶት እየወጣው የነበረው በር ከጀርባው በሃይል ተዘጋ።
አያቱ ነበረች ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ያሳደገችው ሴት አያቱ። አሁን ግን እንደ እንግዳ ከቤት አውጥታ እየጣለችው እንደሆነ አሰበ።
ወንድ አያቱ ሁኔታውን በድንጋጤ ሲመለከት ቆይቶ “ምን እያደረግሽ ነው ? ለምንስ እንዲህ አውጥተሽ ትጥይዋለሽ ? የልጅ ልጅሽ እኮ ነው !” አላት። ሴትዮዋ ምንም ምላሽ አልሰጠችም። ከጓዳ ገብታ ከሰውየው ራቀች። ሁኔታዋ አልገባውም። ግራ ነው የገባው። ሃይለ ቃሏን የሰሙ ጎረቤቶችም በሁኔታው ተደናግረው፤ ምክንያቱ አልገባቸውም።
ልጁ የሴት አያቱ ድምጽ ተመላልሶ እያቃጨለበት በደመ ነፍስ እግሩ ወደመራው መራመድ ጀምሯል። ጧት የለበሰውን እንደለበሰ ነበርና የያዘው ገንዘብም ሆነ ስልክ የለም። እስኪ ጓደኛዬ ዘንድ ልሂድ ብሎ መጀመሪያ ወደ ጓደኛው ሄደ።
“የማደሪያ ቦታ አለህ ?” ሲል ጓደኛው ጠየቀው።
“አይ ከቤት አባረሩኝ” ልጁ መለሰ።
“ወይኔ ይቅርታ። ወላጆቼ ማንም እዚህ እንዲቆይ አይፈቅዱም። ብረዳህ ደስ ይለኝ ነበር፤ ምንም ማድረግ አልችልም”። ሲል ውሳኔውን ነገረው።
ልጁ ጉዞውን ቀጠለ። ሌላኛው ጓደኛው ሲመጣ አይቶታል። “ሁሉም ነገር ደህና ? የተፈጠረ ነገር አለ ?” ልጁን ጠየቀው።
ልጁም “የምሄድበት ቦታ የለኝም ፤ ለጥቂት ቀናት ከአንተ ጋር ብቆይ…” ልመና በሚመስል ድምጽ ጠየቀ።
“እዚህ ምን ልታደርግ ነው ? ገንዘብ የለህም ?” ጓደኛው መልሶ ጠየቀው።
“አይ… ምንም” በለሰለሰ አንደበት መለሰ።
“ይቅርታ አድርግልኝ ፤ እዚህ መቆየት አትችልም።” ቁርጡን አሳወቀው።
ልጁም አንገቱን አቀርቅሮ ወጥቶ ሄደ።
የሴት ጓደኛውን ፈለገ። አቅፎ የደረሰበትን ነገር ሁሉ ገለጸላት። ተጨነቀች ፤ ወላጆቿን ለማነጋገር ሄዳ ድምጿ ጠፍቶ ተመለሰች።
“እዚህ መቆየት እንደማትችል ነገሩኝ ፤ ምንም ማድረግ አልችልም። አዝናለሁ ፍቅሬ ፣ እንደዚህ መሆን አልነበረበትም”።
አሁን ልጁ ብቻውን ቀርቷል። ማንም ሳይኖር ብቻውን። በእግረኛ መንገዱ ዳር በሚገኝ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ ወደ ሰማይ ተመለከተ። በሃሳብ ወጣ ወረደ። ብቻውን ለተውት፣ ምንም ላልሰጡት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሰጥቶ ነበር። ሳያስበው አይኑ እንባ አቀረረ።
ሰዓታት አለፉ። ማንም ሊፈልገው እንደማይመጣ እያሰበ ሳለ ወንድ አያቱ ብቅ አለ።
“ወደ ቤት እንሂድ” አለው።
መሄድ ባለመፈለጉ “ለምን እሄዳለሁ ? እንደገና አውጥታችሁ ልትጥሉኝ ነው ?” የሆነበትን አስቦ ይበልጥ እንባው መጣ።
“እባክህ እመነኝ። ዝም ብለህ ና እንሂድ”።
አያቱን ተከትሎ ምንም ሳይነጋገሩ አብረው መጓዝ ጀመሩ። ከቤት ሲደርሱ ሴት አያቱ ልጁን ልታቀፈው ሮጣ ወጣች። ልጁ ግን ሲያያት ወደ ኋላ ተመለሰ። ወንድ አያቱም ልጁን ጎትቶ አስቀመጠውና በተረጋጋ አንደበት እንዲህ አለው፦
“ሴት አያትህ ይህን ያደረገችው ጨክናብህ አይደለም። ዓይንህን እንድትገልጥ ፣ ነገሮችን እንድታገናዝብ ትፈልጋለች። ኪስህ ሲሞላ ፣ የምትሰጠው ሲኖርህ ብቻ ከጎንህ የሚቆሙትን እንድትመረምር ትፈልጋለች።
በጓደኞች የተከበብህ መስሎህ ነበር። ጠንካራ ግንኙነት እንዳለህ አምነህ ነበር። አንተ ማየት ያልፈለካቸውን ነገሮች እሷ ቀድማ አይታቸዋለች። ስትሰጣቸው ብቻ የሚከቡህን ፣ የሚጠቀሙብህን ፣ አንተ ፈላጊ ስትሆን እነሱ የሸሹህን ስለዚህ አያትህ እውነቱን እንድታይ ማድረግ ነበረባት። ያን ስታደርግብህ ግን ልቧ እያዘነ ነበር ፤ አትፍረድባት።”
ልጁ ማልቀስ ጀመረ።
ሴት አያቱ ቀረብ አለች። “እንዲህ ሳደርግብህ ልቤን ሰብሬ ነው። ውሸትን እንድታምን መፍቀድ ስላልቻልኩኝ ነው፤ በጣም እወድሃለሁ ልጄ።”
አቀፋት። እንደ ህጻንነቱ ሁሉ በጥብቅ አቀፈችው። ከቃላት ሊማረው የማይችል አንድ ነገር ተምሯል።
